የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን  ህያው የጀግንነትና አብሮነት ነፀብራቅ   ነው  

ሚዛን አማን፤  የካቲት 22 / 2016 (ኢዜአ)፡- የዓድዋ ድል  የኢትዮጵያውያን   ህያው የጀግንነት ፣ የአንድነትና  አብሮነት  ነጸብራቅ የሆነ አኩሪ  ገድል መሆኑን በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ምሁራን ገለጹ።

ይህን ጠንካራ የአንድነት ምሶሶ ሲዘከር  በትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመድገምና ብሔራዊ ጥቅሞችን ተባብሮ በማስከበር መሆን እንዳለበትም ምሁራኑ አመልክተዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና ትምህርት ክፍል መምህር ሳሙኤል ጌታቸው እንዳሉት፤ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የማሸነፍ ሥነ ልቦና ብርታት ነው።

አባቶቻችን  የኢትዮጵያን በሉዓላዊነት ለማቆየት ያላቸው ጠንካራ ሥነ ልቦና ነው ብለዋል።

ይህ የአልሸነፍ ባይነት ሥነ ልቦና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነ ገድል መፈጸሙን ጠቅሰው፤  የዛሬ ትውልድ ደግሞ  በልማት  የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጥ አለብን ሲሉ ገልጸዋል።

የድል ታሪክ ለዘመናት እየተዘከረ ሲቆይ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና ውስጥ የጀግንነት ወኔን እየተከለ ነው ያሉት ምሁሩ፤ ይህ ዓይነት ክስተትና ታሪክ ለቀጣይ ትውልድ ጥንካሬ ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።

ዓድዋ ለአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል ሆኖ ያበራና በልዩነት ውስጥ የተፈጠረውን ፍጹም ብሔራዊ አንድነትን ምርኩዝ አድርጎ በመሆኑ አገራዊ ችግሮቻችን ለመፍታት በተናጠል ሳይሆን በአብሮነት መንፈስ መተሳሰርን አለብን ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያን ከፍ አድርጎ ከሚያስጠሩ የጋራ ታሪኮች  መካከል ዓድዋ ግንባር ቀደም መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርስቲው የታሪክ ና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አለማየሁ አብርሃም  ናቸው።



 

ይህ የጋራ ታሪክ እንዲሁ የመጣ ሳይሆን ለኢትዮጵያ በጋራ አስቦ የመቆም አሻራ በጉልህ የደመቀበት በመሆኑ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ለአንድ ዓላማ ተመሳሳይ አስተሳሰብን በሥነ ልቦና ቀርጾ በጋራ መሥራት ለትልቅነት የሚያበቃ ስለመሆኑ ዓድዋ ሕያው ምስክር እንደሆነ አመልክተዋል።

እኛ ኢትዮጵያውያን በብዝኃነት ውስጥ አንድ የሚያደርገን ሥነ ልቦና ያለን ሕዝቦች ነን ብለዋል።

ይህን ጠንካራ የአንድነት ምሶሶ ሲዘከር  በትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ በመድገምና ብሔራዊ ጥቅሞችን ተባብሮ በማስከበር ሊሆን እንደሚገባም  ምሁራኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም