ለአገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማነት የድርሻችንን እንወጣለን---የወላይታ ዞን ነዋሪዎች  

ሶዶ ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ለአገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በወላይታ ዞን በህብረተሰብ ተወካዮች መረጣ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በወላይታ ዞን ከሚገኙ 19 ወረዳዎችና አራት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 2ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጀንዳ ልየታ ላይ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን መርጠዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች እንዳሉት፣ የአገራዊ የምክክር መድረክ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ስለሚያስችል ለውይይቱ ስኬታማነት የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተዋል። 

ለማህበረሰብ ተወካዮች መረጣ ለመሳተፍ ከካዎ ኮይሻ ወረዳ እንደመጡ የገለጹት አቶ ዘለቀ ኩማ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሰላም፣ ልማትና አንድነትን ለማጠናከር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ለስኬታማነቱ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። 

 ተወካዮች መረጣ ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች እንደመምጣታችን ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቅርበት ለመስራት ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል። 

የህብረተሰብ ተወካይ በመሆኔ በምክክር መድረኩ መሠረታዊ የሆኑ አገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ መግባባት እንዲፈጠርና የኮሚሽኑም ግብ እንዲያሳካ የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።

ከኦፋ ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ወርቅነሽ ጫንቆ በበኩላቸው እንደአገር ሰላምና ሁለንተናዊ ልማትን ለማረጋገጥ አገራዊ ምክክሩ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ይበል የሚያሰኙ ናቸው። 

ለእርስ በርስ አለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደአገር የተጀመሩ ሥራዎች ስኬታማ እንዲሆኑም ለኮሚሽኑ ሥራ ስኬታማነት ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

በህብረተሰብ ተወካዮች ምርጫ ላይ በንቃት ከመሳተፍ ባለፈ ልዩነትን እየፈጠሩ ያሉ የህዝብ አገራዊ ጉዳዮችን ለአጀንዳ በመለየት ተሳትፏችውን እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል።  

አለመግባባቶችን ተወያይቶ በጋራ ለመፍታት የሚያስችል የመፍትሔ ሀሳብ በማምጣት ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን የበኩሉን ለመወጣት መዘጋጀቱን የገለጸው ደግሞ የገሱባ ከተማ ነዋሪ ወጣት አክሊሉ ደሳለኝ ነው። 

የአካባቢው ማህበረሰብ የምክክር መድረኩ ገለልተኛና አካታች መሆኑን ተገንዝቦ በወከለው አካል አማካኝነት በንቃት እንዲሳተፍ በማድረግ በኩል ሚናውን እንደሚወጣ ተናግሯል። 

 

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸው እንዳሉት ኮሚሽኑ በህዝቦች መካከል የሚስተዋሉ ልዩነቶችና አለመግባባቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል አሳታፊ የምክክር መድረክ የማመቻቸት ስራ በገለልተኝነት እየሰራ ነው። 

ለዚህም በወላይታ ዞን ከሚገኙ 19 ወረዳዎችና አራት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 2 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች በአጀንዳ ማሰባሰብ የሚሳተፉ ተወካዮቻቸውን መረጣ ላይ ተሳትፈዋል።

ከተለያዩ ማህበራዊ መሰረቶች የመጡት ተሳታፊዎች ከወረዳዎቹና ከከተማ አስተዳደሮቹ በጠቅላላው 600 የህብረተሰብ ተወካዮችን መምረጣቸውንም ዶክተር ዮናስ ገልጸዋል።  

ላለፉት አራት ቀናት በተመሳሳይ በጌዴኦ ዞን በምክክሩ የሚሳተፉ የህብረተስብ ተወካዮች መረጣ መካሄዱን ጠቅሰው፣ በሚቀጥሉት ሳምናታትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቀሪ 10 ዞኖች የልየታ ሥራው እንደሚከናወን ዶክተር ዮናስ አመልክተዋል። 

በመሆኑም ኮሚሽኑ የማህበረሰብ ተወካዮች መረጣና ሌሎች በርካታ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፣ የተጀመሩ ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ኮሚሽኑ በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የወላይታ ዞን ተወካዮችን መረጣ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም