የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅር እና አንድነት ለስኬት እንደሚያበቃ ጎልቶ የታየበት ነው -ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅር እና አንድነት ለስኬት እንደሚያበቃ ጎልቶ የታየበት ነው -ምሁራን
ሀዋሳ/አርባ ምንጭ/ ቦንጋ፤ የካቲት 22 /2016 (ኢዜአ) ፡-የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅር እና አንድነት ለስኬት እንደሚያበቃ ጎልቶ የታየበት ነው ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።
የዛሬ 128 ዓመት የካቲት 23 ቀን በእለተ እሁድ ነበር በዓለም ፖለቲካ በዘር ላይ የተመሰረተውን ኢሰብአዊ ግንኙነት የለወጠና ኢትዮጵያን ከፍ ያደረገ ደማቅ ታሪክ የተመዘገበው።
ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆና በእብሪት ተወጥሮ በጄነራል አልቤርቶኒ እየተመራ የመጣውን የቅኝ ግዛት ተስፋፊ ጦር ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንዳቸው ድል በመቀዳጀት በየትውልዱ ሲታወስ የሚኖር ገድል አስመዝግበዋል።
ከጫፍ እስከ ጫፍ ያሉት ኢተዮጵያዊያን የተላለፈላቸውን የክተት አዋጅ ተቀብለው በአንድነት በማበር ለመላው ጥቁር ህዝብ አርአያ የሆነ የድልና የአሸናፊነት ታሪክ በዓድዋ ተራራ ላይ በደማቸው ጽፈዋል።
የዓድዋ ድልን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋጋራቸው የሃዋሳ፣ የአርባ ምንጭና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም፣ የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅር እና አንድነት ለስኬት እንደሚያበቃ ጎልቶ የታየበት ነው ይላሉ።
ድሉ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስከበረ አኩሪ ታሪካችን እንደሆነም ነው ምሁራኑ የገለጹት።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቨርናንስና ልማት ጥናት ክፍል መምህር ዮሴፍ ዋቴ እንዳሉት፣ አድዋ በነጭ ወራሪዎች ላይ ድል መቀዳጀት በማይታሰብበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በጀግንነት ደማቅ ታሪክ የጻፉበት ክስተት ነው።
የዓድዋ ድል ሁሉንም ኢትዮጵያውያን አንድ ከማድረግ ባለፈ ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሀገር ፍቅር ቀድሞ የታየበት ትልቅ የአብሮነት እሴት መሆኑንም ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል መላው ጥቁር ህዝብ ለነጻነቱ እንዲነቃቃ ማድረጉንም የገለጹት መምህሩ፣ በየዓመቱ ለድሉ እየተሰጠ ያለው ትኩረት መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።
ድሉ ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በቋንቋና በዕምነት ያላቸውን ልዩነት ትተው ለሀገር በጋራ ስለቆሙ የመጣ መሆኑንና ለዛሬው ትውልድም ይሄን የአሸናፊነት ምስጢር በአግባቡ ማስረጽ እንደሚገባ ተናግረዋል።
መምህር ዮሴፍ እንዳሉት ለድሉና ለድሉ ባለቤቶች ተገቢ ክብር መሰጠቱ ሊጠናከር ይገባል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ሀላፊና መምህር ያምራል መኮንን በበኩላቸው እንዳሉት፣ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻቸውን ትተው ለሀገር ክብር በጋራ በጀግንነት የተዋደቁበት ነው።
የዛሬው ትውልድም ከዓድዋ ድል የአንድነትና የከፍታ ታሪክ በመማር ለሀገር ሰላም፣ አንድነትና የብልጽግና ጠንክሮ መስራት እንዳለበት መክረዋል።
"ዓድዋ ከሌሎች ድሎች የተለየና የኢትዮጵያ ከፍታ የታየበት ነው" ያሉት ደሞ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ሰለሞን ኪዳኔ ናቸው።
የህዝቦች የተባበረ ክንድ ውጤት የሆነው የዓድዋ ድል የአፍሪካ ሀገራትም ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ መንገድ የከፈተ ነው ብለዋል።
መምህሩ እንዳሉት ዛሬ ድረስ በቅኝ ገዠዎች ሳትደፈር በነጻነቷ ጸንታ ከነክብሯ የቆየቸው ኢትዮጵያ የደምና የህይወት መስዋዕትነት የተከፈለባት መሆኑን በመገንዘብ፣ ለኩራታችንና ለአሸናፊነት መሰረት ለሆነው የዓድዋ ድል የሚሰጠው ትኩረት መቀጠል አለበት።
የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ የድል ምስጢር ተምሮ ሀገርን ከድህነት ለማውጣትና ለማሻገር በአንድነት እንዲቆምም አሳስበዋል።
በዓድዋ ድል ሴቶች የላቀ ተሳተፎም በጉልህ መጠቀስ ያለበት ዐቢይ ጉዳይ መሆኑን አውስተው፤ በተለይ ጦሩን በማጀገን፣ ስንቅ በማሰናዳት፣ ቁስለኛን በማከም፣ በመዋጋትና የጦር መሪ በመሆን ጭምር ታላቅ ሚና እንደነበራቸውም መምህር ሰለሞን አስረድተዋል።
ይህም በሀገር ጉዳይ የማይመለከተው ሰው እንደሌለ ለትውልድ እንደሚያስተምር ጠቅሰው፤ "ዛሬም ልዩነትን ወደጎን በመተው በአባቶች የጀግንነት ወኔ ለሀገር ልማት በጋራ ልንቆም ይገባናል" ብለዋል።
ምሁራኑ እንዳሉት የዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶችና አያቶቻችን ህብረታቸውን በማጠናከርና በጋራ ተሰልፈው ያስመዘገቡት ደማቅ ታሪክ መሆኑን ማጉላትና ትውልዱም ተምሮ እንዲተገብረው ማድረግ ይገባል።
የእዚህ ትውልድ ዓድዋ መሆን ያለበት ልዩነትን ትቶ ድህነትን በማሸነፍ ኢትዮጵያን በማበልጸግ ወደፊት ማምጣት ነው።
ትውልዱ ከዓድዋ የከፍታ ታሪክ ተምሮ ሀገርን ከፍ የሚያደርግ የራሱን ስራ ሰርቶ ማለፍ አለበት።
በዓድዋ መንፈስ ሆኖ፤ በድሉ ብስራት ጠንክሮ ሀገር የምትጠብቅበትን የራሱን ደማቅ ታሪክ መስራት መቻልም ይኖርበታል።