ቀጥታ፡

ልማት ባንክ የክልሉን ኢንቨስትመንት በሚገባ ሊደግፍ ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሐሰን

አሶሳ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ኢንቨስትመንት በሚገባ ሊደግፍ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ጠየቁ።

የክልሉ ከፍተኛ የአመራር አባላት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር በአሶሳ ከተማ መክረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሐሰን በዚሁ ወቅት እንዳሉት ክልሉ ለግብርና የሚውል ሰፊ ለም መሬት እና በርካታ የማዕድን ሀብት ያለው ቢሆንም ባለው አቅም ልክ አለመልማቱን ተናግረዋል።

ምክንያቱ ደግሞ ዘመናዊ እና የተሻሻሉ የማምረቻ ግብአቶች አለመሟላት መሆኑን አስታውሰው፤ ለእምቅ ሀብቱ ልማትና ለኢንቨስትመንቱ መስፋፋት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ክልሉን በሚገባ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ባንኩ በክልሉ ለሚገኙ አልሚ ባለሃብቶች የገንዘብ ብድር አቅርቦትን ጨምሮ አስፈላጊ ድጋፎችን በማመቻቸት የተፈጥሮ ሃብቱ የክልሉን ህዝብ ህይወት ከመቀየር ባለፈ ለሀገር ኢኮኖሚ እንዲውል የማድረግ ሚናውን እንዲጫወት ጠይቀዋል።

የክልሉ መንግስት በበኩሉ ያለውን ሀብት ማልማት እንዲቻል ለበርካታ ማህበራት ኢንተርፕራይዞች እና ግለሰቦች የእርሻ ትራክተር፣ የወርቅ ማሽኖች እና ሌሎች ግብአቶችን ለማቅረብ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው በበኩላቸው ባንኩ ክልሎችን ለመደገፍ የሚያደርገው ጥረት እንዳለ አመልክተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከሁለት ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞችን አሰልጥኖ ድጋፍ ለማድረግ የተጀመረ ጥረት ቢኖርም በሚፈለገው ልክ ውጤት ተገኝቶበታል ማለት እንደማይቻል ጠቅሰዋል።

በቀጣይ ክልሉን ተጠቃሚ ለማድረግ በተለይም ወጣቶችን ጨምሮ በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ባንኩ የሀገሪቱን ህጋዊ የፋይናንስ አካሄድ ተከትሎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በዚህም የብድር አቅርቦት፣ ስልጠናና የምክር አገልግሎትን ጨምሮ ከባንኩ የሚጠበቁ ድጋፎችን ሁሉ እንደሚያካትት ዶክተር ዮሐንስ አመልክተዋል።

ፍትሃዊነት የልማት ዋነኛ መሠረት እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው ለሌሎች ክልሎች የሚደረጉ የኢንቨስትመንት እገዛዎች ሁሉ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም እንደሚደረጉ አረጋግጠዋል።

የክልሉ መንግስትም አልሚ ባለሃብቶችን በሚገባ በመለየት ከማቅረብ ጀምሮ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት በብድር አሰጣጥ ሂደት ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ ለባንኩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ገልጸዋል።

ሌሎች ብድር ጠያቂ አካላትም የአዋጪነት ጥናትን ጨምሮ ከፖሊሲዎች ጋር የሚጣጣሙ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን ማቅረብ እና ህጋዊ አካሄድን አሟልተው እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

ልማት ባንኩ ዛሬ አሰዓት በኋላ በክልሉ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም