አድዋ ለእኛ ለአፍሪካዊያን ኩራታችን ነው - ዶክተር ድላሚኒ ዙማ - ኢዜአ አማርኛ
አድዋ ለእኛ ለአፍሪካዊያን ኩራታችን ነው - ዶክተር ድላሚኒ ዙማ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ አድዋ አፍሪካዊያን በኩራት እንዲቆሙ ያስቻለ ትልቅ ድል መሆኑን የቀድሞ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ድላሚኒ ዙማ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ድላሚኒ ዙማ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን የኩራትና የአህጉሪቱ ሕዝቦች ቀና ብለው እንዲሄዱ ያስቻለ ታሪካዊ ድል ነው።
ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ሥር አለመውደቋ እኛ አፍሪካዊያን እንድንኮራ አድርጎናል፤ በዚህም ኢትዮጵያ የአህጉሪቷ ማዕከል እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአድዋን ሌጋሲ የማስቀጠል ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባትም ነው ያስገነዘቡት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ በልማት፣ ሰላምን በማስጠበቅና በሌሎች ጉዳዮች ከቀዳሚ አገራት ተርታ የምትጠቀስ መሆኗን ገልጸው ይህንን ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የቀደሙት አፍሪካውያን አባቶች አንድነት ከተናጠላዊ ጉዞ በላይ ኃይል እንዳለው በእጅጉ እንደሚገነዘቡ ተናግረው፤ ይህንን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአፍሪካ የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ኃሳብ ለማስረጽ አፍሪካውያን ወንድማማችና እህትማማች መሆናቸውን ሊያውቁ እንደሚገባም ነው የጠቀሱት።
የአህጉሪቱ ሕዝቦች በአንድነት መቆም ከቻሉ አህጉሪቱ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይቻላል ብለዋል።
የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብን ይበልጥ ለማጠናከር አገራቱ የአፍሪካን ታሪክ በየትምህርት ቤቱ በአግባቡ ሊያስተምሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በአህጉሪቱ አሁን ላይ ያለው የትምህርት ሥርዓት ከቅኝ ግዛት ትርክት ያልተላቀቀ መሆኑን አንስተው ይህ ከመሰረቱ ሊቀየር እንደሚገባው ነው የገለጹት።
የ128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል በነገው ዕለት በተለያዩ መርኃ ግብሮች ይከበራል።