አባቶች በዓድዋ ጦርነት በአንድነት ያስመዘገቡትን ድል ትውልዱ አንድነቱን በማረጋገጥ ሊያከብረው ይገባል - የምዕራብ ጎንደር አባት አርበኞች - ኢዜአ አማርኛ
አባቶች በዓድዋ ጦርነት በአንድነት ያስመዘገቡትን ድል ትውልዱ አንድነቱን በማረጋገጥ ሊያከብረው ይገባል - የምዕራብ ጎንደር አባት አርበኞች
|
|
||
መተማ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፡-አባቶች በዓድዋ ጦርነት በአንድነት ሆነው በወራሪው ኃይል ላይ ያስመዘገቡትን ድል በመገንዘብ የአሁኑ ትውልድ ሰላምና አንድነቱን በማረጋገጥ ሊያከብረው እንደሚገባ የምዕራብ ጎንደር ዞን አባት አርበኞች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው አባት አርበኞች እንደተናገሩት ወጣቱ ትውልድ በአንድነትና በሀገር ፍቅር ከተገኘ ከዓድዋ ድል በመማር በጊዜው ህዝባዊ አንድነትንና ሰላምን ለማምጣት ድርሻውን መወጣት አለበት።
አባት አርበኛ በቀለ ጀመረ የዓድዋ ድል የዓለም ጥቁር ህዝብ ሁሉ የኩራት ምንጭ የሆነው በጥልቅ የሀገር ፍቅር በተከፈለ መስዋዕትነት የተገኘ ደማቅ ታሪክ መሆኑን አስታውሰዋል።
የአባቶቻችን የአንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት በአሁኑ ትውልድ አድጎና ጎልብቶ መውጣት እንዳለበት ገልጸው፤ ለዚህም የውስጥ ሰላምና አንድነትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
በእውነት ላይ የተመሰረተ አንድነትና ትብብርን መከተል የወጣቱ ትውልድ መንገድ መሆን እንደሚገባውም አባት አርበኛ በቀለ አመላክተዋል።
አርበኛ በቀለ አክለውም ''እኛ እና እነሱ መባባልን በማስወገድ ለአንዲት ጠንካራና ለጥቁሮች ሁሉ ቤዛ የሆነች ሀገር መገንባት የመንግሥት ብቻ ሳይሆን፤ የመላ ህዝቡ መሆኑን በመረዳት ሁሉም ድርሻውን መወጣት አለበት'' ብለዋል።
ሌላኛው አባት አርበኛ ባይተኩስ ኪዳኑ በበኩላቸው፤ ሀገሪቱን እየፈተኑ ያሉትን የአንድነት መሸርሸርና ውስጣዊ ሰላም ማጣትን ከአባቶች ጥበብ በመማር ማለፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
"አርበኝነት ጠላትን ድል መምታት ነው" ያሉት አባት አርበኛው፤ ጠላት የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለመከፋፈልና ሀገርን ወደ ትርምስ ለማስገባት የሸረበውን ዓላማ ማክሸፍ ይገባናል ሲሉም ምክራቸውን አስተላልፈዋል።
የራስን ጥቅም ከህዝብ ጥቅም የሚያስቀድም ትውልድ የታሪክ ተወቃሽ መሆኑን ገልጸው፤ ትውልዱ ቆም ብሎ በማሰብ አካሄዱን እንዲያስተካክል መክረዋል።
ሀገሪቱ የገጠሟትን ችግሮች ለመወጣት በሚደረገው ጥረት ሚናቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም አባት አርበኛ ባይተኩስ አስታውቀዋል።
"መተማመን፣ እርስ በእርስ መዋደድና ለጠላት አለመደፈር የእኛ የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ ነው" ያሉት ደግሞ ሌላኛው አባት አርበኛ የሺጥላ አደናግር ናቸው።
በመሆኑም ያለፈው ትውልድ በባዶ እግር ሄዶ በደምና አጥንታቸው ያስከበሯትን ሀገር ለቀጣዩ ትውልድ ከነ ሙሉ ክብሯ ማስተላለፍ ይገባዋል ብለዋል።
ወጣቱ ለሀገሩ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ ሆኖ እንዲንቀሳቀስም ጠይቀዋል።
በአማራ ክልል 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።