ቀጥታ፡

ምሁራን ለስኬታማ ሀገረ መንግስት ግንባታ አዎንታዊ ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ምሁራን ትውልድን በመቅረጽ ለስኬታማ ሀገረ መንግስት ግንባታ አዎንታዊ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። 

አድዋን ለዘላቂ ሠላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሠላም ንቅናቄ የምክክር መድረክ የማጠቃለያ መርሃ ግብር በማካሄድ ላይ ይገኛል።


 

በዚሁ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ባለቤትና የማንነታችን መገለጫ ነች ብለዋል።

ነገር ግን በኢትዮጵያ የተከሰቱ የድህነትና በእርስ በእርስ ግጭቶች ያላትን ገናና ታሪክ እያሳነሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ሀገሪቱ  እያጋጠማት ያለውን ችግር ለማስተካከልም የአሁኑ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

በአድዋ የድል ታሪክም ያልተጠናቀቀውን የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትን በብልሃት፣ በጥንቃቄና በትዕግስት ዕውን ማድረግ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

ምሁራን ዜጎች የተረጋጋ ሂወት እንዲኖራቸው የአንበሳውን ድርሻ መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።

የትምህርት ሥርዓቱንም በማሻሻል የተረጋጋች፣ ለዜጎቿ የተመቸች፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የሀሳብ መሪነት ሚና የምሁራን ድርብ ኃላፊነት እንደሆነም ተናግረዋል።

የወደፊቱን ትውልድ ማንነት በመቅረጽ፣ ኢኮኖሚያዊ ልማትን የሚያሳልጡ ጉልበቶችን መስጠትና ዘላቂ ስርዓት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ወጣቶችም ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነትን በማስቀደም የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል  ብለዋል።

የኃይማኖት ተቋማትም ለጋራ እሴት መሰረት በመሆናቸው ለሀገረ መንግስት ግንባታ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ መቻቻልና አብሮነት መጎልበት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የአድዋ ድል ቱሩፋቶችንም ለቱሪስት ልማትና ለውጤታማ ሀገረ መንግስት ግንባታ እንዲውል ወደ እሴት መቀየር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

የዘንድሮው 128ኛ የዓድዋ ድል በዓልም ነገ ቅዳሜ የካቲት 23/2016 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርበኞች እና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በተገኙበት በድምቀት የሚከበር ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም