ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል የተገኘው በኢትዮጵያውያን ፍቅር፣ ሕብርና ትብብር ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል በኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅር፣ በህብረ ብሔራዊ አንድነትና ጠንካራ መተባበር የተገኘ ተምሳሌታዊ ድል መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ዓድዋ ዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማጠቃለያ መርኃ ግብር በዓድዋ የድል መታሰቢያ በመካሄድ ላይ ነው።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚህ ጊዜ እንዳሉት፤ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ጦርነት በተባበረ ክንዳቸውና በአልገዛም ባይነት ወኔያቸው ወራሪ ኃይልን በማንበርከክ የሀገራቸውን ክብር አፅንተዋል።

የዓድዋ ድል በህብር፣ በፍቅርና በትብብር የተገኘ ግዙፍ ድል መሆኑን ጠቅሰው፥ የወቅቱ የኢትዮጵያ ጦር በህብረ ብሔራዊ አንድነት የተዋቀረ ሃይል መሆኑንም አንስተዋል።

የዓድዋ ዘማቾች ህብርነት የብሔር ብቻ ሳይሆን የመሪና የህዝብ፣ የክርስቲያንና የሙስሊም፣ የከያንያንና የስንቅ አዘጋጆች፣ ሴቶች እና መላ ኢትዮጵያውያን ህብረት በመፍጠር ለሀገር ክብር የተመሙበት  መሆኑንም ገልጸዋል።

ዛሬም የኢትዮጵያን ጠላቶች ለማንበርከክ፣ ድህነትን ድል ለማድረግና ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለማሸነፍ ህብር ሆኖ መዝመት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የዛሬዋን ኢትዮጵያ የምግብና የሳይበር ሉዓላዊነት ለማረጋገጥና ሀገርን ለማፅናት ሁሉም በጋራ መሰለፍ እንዳለበት በማንሳት።

በዓድዋ ዘመን የታየው የሀገርና የወገን ፍቅር ዛሬም ፀንቶ እንዲቀጥል መሥራት ይጠበቃል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሀገር የሚከፈል ዋጋ ከምንም በላይ ነው ብለዋል።

የዓድዋ ዘመን ጀግኖች የተለያየ ቋንቋ እየተናገሩ፣ የተለያየ ሃይማኖት እየተከተሉ፣ በአንድነት የዘመቱት ለሀገር ከመተባበር የሚበልጥ ነገር እንደሌለ ስለተገነዘቡ መሆኑንም አብራርተዋል።

ዓድዋ ሀገር የሚታደግና የሚያጸና ትምህርት ቤት መሆኑን ጠቅሰው፥ ስብራቶችን ለመጠገን ፍቱን መድሃኒት እንደሆነም አክለዋል።

በመሆኑም  ከቀደምት ጀግኖች የሀገር ፍቅርን በመውረስ ለሀገር ሰላምና ብልፅግና እንዲሁም ለማይናወጥ ሀገረ መንግስት ግንባታ መትጋት የዚህ ዘመን ትውልድ ሃላፊነት ነው ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም