ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን መቀላቀል በምትችልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደረገ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን መቀላቀል በምትችልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ተደርጓል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪ ገብረመስቀል ጫላ ከ13ኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የሚኒስትሮች ጉባኤ ሊቀመንበርና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የወጪ ንግድ ሚኒስትር ዴኤታ ታሂኒ ቢን አሕመድ አል ዜዮዲ ጋር መክረዋል።

በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት ምክትል ተደራዳሪ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶር)፣ የተደራዳሪ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም በተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ኡመር ሁሴን ተሳትፈዋል።


 

የልዑክ አባላቱ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል የተደረጉ ድርድሮችንና እስከ አሁን የተሄደበትን ርቀት ያብራሩ ሲሆን የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ኢትዮጵያ ድርጅቱን እንድትቀላቀል ድጋፍ እንድታደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ልዑኩ ከዩናይትድ ኪንግደም የንግድ ፖሊሲ ሚኒስትር ዴኤታ ግሪጎሪ ዊሊያም ሀንድስ እና በድርጅቱ የኢትዮጵያን ጉዳይ ከሚከታተለው ኮሚቴ ሊቀመንበር እና በጄኔቫ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ሬቤካ ፊሸር ላምብ ጋር መክረዋል።


 

ዩናይትድ ኪንግደም ልዑክ አባላቱ ኢትዮጵያ ድርጅቱን እንድትቀላቀል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩና በጉዳዩ ዙሪያ ኢትዮጵያን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል።

በተለይ በድርጅቱ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚከታተለው ኮሚቴ ሊቀመንበርና በጄኔቫ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ሬቤካ ፊሸር ላምብ ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላቀል የቀሩ ድርድሮችን በብቃት እንደምትወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶችና የዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያ ድርጅቱን ለመቀላል እያደረገች የምትገኘውን ጥረትና የተሄደበትን ርቀት አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን መቀላቀሏ በሀገሪቱ የንግድ ምጣኔና ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም