የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለፀ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ኛው አጠቃላይ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለፀ።
ቦርዱ በ6ኛው ዙር ቀሪ እና ድጋሚ ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከሲቪክ ማህበራት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላትወርቅ ኃይሉን ጨምሮ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች እና ሲቪክ ማህበራት ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሜላተወርቅ ኃይሉ በዚሁ ጊዜ 6ኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ ስኬታማ በሆነ መልኩ መካሄዱን አስታውሰው፥ ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ አፋር፣ በሶማሌ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫ ለማካሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅድመ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን አመላክተዋል።
በዚህም በ29 የምርጫ ክልሎች እና በ1 ሺህ 146 የምርጫ ጣቢያዎች ዘጠኝ ለተወካዮች ምክር ቤት እና 26 ለክልል ምክር ቤት ተወካዮችን ለመምረጥ ምርጫው እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ይህንን አስመልክቶ ቦርዱ ከሚመለከታቸው ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማህበራት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ተከታታይ ውይይቶችን እና ምክክሮችን ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዛሬው የውይይት መድረክም የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ለፓርቲዎች እና ለሲቪክ ማህበራት ቀርቦ ውይይት እየተካሄደ ነው።