የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ልዕልና ለማስጠበቅና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ትልቅ መሰረት ነው - ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ልዕልና ለማስጠበቅና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ትልቅ መሰረት ነው - ምሁራን
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2016(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል በሁሉም መስክ ልዕልናዋ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለማስቀጠልና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ትልቅ መሰረት መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ገለጹ።
አውሮፓውያን በበርሊን ኮንፈረንስ አፍሪካን ለመቀራመት በተስማሙት መሰረት የጣሊያን ወራሪ ኃይል ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ስር አድርጎ ለመበዝበዝ አልሞ ነበር።
በእብሪት ባህር አቋርጦ የመጣው የጣሊያን ወራሪ ጦር ስለሰብዓዊ ክብርና ሉዓላዊነት በተግባር ተፈትነው ያለፉ ኢትዮጵያውያን ላይ ጦር መዘዘ።
ጀግንነት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነት፣ እንዲሁም የአልገዛም ባይነት ወኔን የታጠቁ ኢትዮጵያውያን በብልህ መሪዎቻቸው አስተባባሪነት ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቆ የመጣውን ወራሪ ጦር በሶሎዳ ተራሮች ግርጌ ቅስሙን በመስበር የሃገራቸውን ክብርና ነጻነት አጸኑ።
ኢትዮጵያውያን ግዙፍ በሆነው የዓድዋ ድላቸው ለጭቁን አፍሪካውያን እንዲሁም ለተገፉ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነጻነት የትግል ንቅናቄን አዋልደዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማህዲ እንዳሉት፥ የዓድዋ ድል የዓለም የኃይል ሚዛን ዕይታን የለወጠ የታሪክ እጥፋት ነው።
ድሉ ብዝኃ ማንነት ባላቸው ኢትዮጵያውያን አንድነት፣ ፅናትና ጀግንነት የተገኘ ከመሆኑም በላይ ለአፍሪካውያን የነጻነት ምሳሌ መሆኑ ታሪካዊ እሴቱን ግዙፍ ያደርገዋል ነው ያሉት።
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አብርሃም አረፈዓይኔ በበኩላቸው፥ የዓድዋ ድል ሚስጥር የሀገር ፍቅርና ህብረ ብሔራዊ አንድነት መሆኑን ተናግረዋል።
ድሉ ኢትዮጵያዊ ወኔ እና የአሸናፊነት መንፈስ በገቢር የታየበት በዓለምም የኢትዮጵያን ልዕልና የገለጠ ነው ብለዋል።
በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የስነዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ግርማዬ ዓለማየሁ፥ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ ከቅርብ እስከ ሩቅ ያሉ ወራሪዎች ቢሞክሯትም አንድም ጊዜ ያልተንበረከከች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
የዓድዋ ድልም አፍሪካን ለመቀራመት የቅኝ ግዛት ቀንበርን በብዙ ሀገራት የጫኑ አውሮፓውያንን ክብር የገፈፈ እና የጥቁሮችን አሸናፊነት በአዲስ ምዕራፍ የጻፈ ኢትዮጵያዊ ገድል መሆኑን አንስተዋል።
ምሁራኑ ከዓድዋ ድል ለሀገር ክብርና ልዕልና ዛሬም በአንድነት መነሳትን፣ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች መትጋትን መማርና በተግባር ማሳየት የዚህ ዘመን ትውልድ አደራ ነው ብለዋል።
ድሉ የምንመኛትን የበለጸገች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት ትልቅ መሰረት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የወል ትርክትን በመገንባት፣ ፖለቲካዊ የሀሳብ ልዕልናን በማጉላት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንባት የዘመኑን ዓድዋ በፅኑ መሰረት መጻፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።