የፋይናንስ ተቋማት ለፋይናንስ ትምህርት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የፋይናንስ ተቋማት ለፋይናንስ ትምህርት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦ የፋይናንስ ተቋማት በክህሎት ላይ የተመሠረተ የፋይናንስ አጠቃቀምን ለማሳደግ ለደንበኞች የፋይናንስ ትምህርት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ "ከፈርስት ኮንሰልትና ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን" ጋር በመተባበር ብሔራዊ የወጣቶች የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ትምህርት ሞጁል መርሃ -ግብር ይፋ አድርጓል።
የማስተማሪያ ሞጁሉ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የፋይናንስ ክህሎት በማጎልበት የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ የሚረዳ ነው።
የወጣቶችን እና ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ክህሎት በማሳደግ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔና ዘላቂነት ያለው የስራ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አማካሪ ማርታ ኃይለማሪያም፤ ባንኩ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የግንዛቤ ደረጃ በማሳደግ የፋይናንስ አካታችነትና የዘርፉን ጤናማነት ለመጨመር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የማስተማሪያ ሞጁሉም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በመላ አገሪቱ በፋይናንስ ተቋማት፣ በመንግሥትና በልማት ድርጅቶች በተናጠል እየተከናወነ ያለውን የፋይናንስ ትምህርት ወጥነትና ቀጣይነት ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
የቁጠባ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፣ ብድር፣ የበጀት አዘገጃጀትና ሌሎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን ሞጁሉ የሚሸፍን መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የፋይናንስ ተቋማት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲዳብር መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በዛሬው እለት ይፋ የሆነው ሞጁል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 የፋይናንስ አገልግሎት ላይ ግንዛቤ ያላቸውን ወጣቶች፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ወደ 75 በመቶ ለማድረስ እየተከናወነ ያለውን ተግባር የሚያግዝ መሆኑም ተመላክቷል።
የፈርስት ኮንሰልት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ነቢል ቀሎ፤ ባንኮችና አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂና ሌሎች አማራጮች ለበርካታ የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ እየሆኑ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የገጠሩ ማኅበረሰብ፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችንም የህብረተሰብ ክፍሎች የፋይናንስ አስተዳደርና አጠቃቀም ክህሎት ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የማስተርካርድ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ሳሙኤል ያለው፤ ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ የፋይናንስ አጠቃቀም ክህሎት ላይ የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የፋይናንስ ተቋማት ደንበኞቻቸው በእውቀትና ችሎታ ላይ የተመሰረተ የፋይናንስ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ግንዛቤ መፍጠር ይገባቸዋል ተብሏል።