ቀጥታ፡

ከአድዋ ድል ተምረን  የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት  ማፅናት  አለብን 

ደሴ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፡- ችግሮችን በንግግርና በምክክር በመፍታት  የኢትዮጵያን ሰላምና  አንድነት በጋራ  ማፅናት አለብን ሲሉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ ገለጹ፡፡

"የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ዓርማ" በሚል መሪ ሀሳብ 128ኛውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ዛሬ በደሴ ከተማ ተከብሯል።

ዶክተር መንገሻ አየነ በወቅቱ እንደተናገሩት፤  የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት፣ የአንድነትና የአሸናፊነት ዓርማና ምልክት ነው፡፡

ቀደምት አባቶች  በአንድነት ሆነው አድዋ ላይ ከተጎናጸፉት አኩሪ ድል  ተምረን የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በጋራ ማፅናት አለብን ሲሉ ገልጸዋል። 

ችግሮችን በንግግርና ምክክር በመፍታት የኢትዮጵያን  ጥቅም በማስቀደም በጋራ  መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡


 

ዩኒቨርሲቲውም የኢትዮጵያን አንድነት፣ የፍቅርና የሰላም ባህልና እሴት በማስተማር ትውልዱ ሀገሩን እንዲያስቀጥል ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ አቶ ይድነቃቸው ጌታነህ በበኩላቸው፤ አድዋ የሁላችንም አባትና እናቶች የጋራ የድል ታሪክ በመሆኑ በኩራት መኖር እንድንችል ያስቻለ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ለውጭ ጠላት ሳንንበረከክ በክብራችን ቀና ብለን እንድንሄድ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ነው፤ ከዚህ   ትምህርት ወስደን አንድነታችንና ሰላማችንን በጋራ ማስጠበቅ ይኖርብናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለአድዋ ድል መነሻ የሆኑ በዞኑ  "ይስማ ንጉስ" እና "ወረኢሉን" ጨምሮ ሌሎችም ታሪካዊ ስፍራዎች እንዳሉ ጠቅሰው፤ ስፍራዎቹ የቱሪዝም መስህብ ሆነው  ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ ድል ተምሮ ሀገሩን መጠበቅና ሉዓላዊነቱን ማስቀጠል ይኖርበታል ያሉት ደግሞ  አባት አርበኛ ሀምሳ አለቃ ባለሟል መለሰ ናቸው፡፡

በጥቃቅን ጉዳዮች እርስ በእርስ ከመነታረክ ወጥቶ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንደሚገባ ጠቁመው፤ ወጣቱ የራሱን ታሪክና ድል ማስመዝገብ እንደለበት ተናግረዋል፡፡


 

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ ፤  የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ጀግንነት፣ አትንኩኝ ባይነትና ከፍታ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዘመናችን የየራሳችንን ታሪክና ድል በማስመዘግብ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት ማስመዝገብ ይኖርብናል ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ህብረተሰቡም ሰላሙንና አንድነቱን ጠብቆ  የኢትዮጵያን ከፍታ ማረጋገጥ እንዳለበትም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲና የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ በመተባበር ባዘጋጁት በዓል የአመራር አባላት፣  አባት አርበኞች፣ የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎችም  አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም