ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካና አፍሪካ ቀንድ አገራት ወጥ የሆነ የፍልሰተኞች የአሰራር ማዕቀፍ መዘርጋት እንዳለባቸው ተገለጸ

 አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካና አፍሪካ ቀንድ አገራት ዜጎች መብታቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርግ የተጣጣመ የፍልሰተኞች የአሰራር ማዕቀፍ ሊዘረጉ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በቀጣናው ዜጎች በተለያዩ አገራት ሄደው መስራት የሚችሉበትን ተመሳሳይ የትምህርትና ስልጠና ስርዓት የመቅረጽ ስራ መጀመሩ ተጠቁሟል። 

ከየካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 5ኛው የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች የሚኒስትሮች ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።


 

ፎረሙ "የመደበኛ ፍልሰት ትሩፋቶች ለወጣቶች የሥራ ዕድል፣ ለክህሎት ልማት እና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ" በሚል መሪ ሀሳብ ሲከናወን ቆይቷል።

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የፎረሙ አባል አገራት፣ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት(አይኤምኦ)፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ እና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካዮችና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያ ፎረሙን ላለፉት ሁለት ዓመታት በሊቀ መንበርነት መርታለች። 

የፎረሙ አባል አገራት በቀጣናው ዜጎች በተለይም ወጣቶች ስራ ለማግኘት የሚያደርጉት እንቅሰቃሴ ደህንነቱ የተጠበቀ፣መደበኛና ሰብዓዊነት የተሞለባት እንዲሆን ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ማድረጋቸው ተገልጿል።

በምስራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ቀንድ ይኖራል ተብሎ ከሚገመተው 170 ሚሊዮን ሕዝብ መካከል 60 ሚሊዮን የሚጠጋው ከ15 እስከ 24 የእድሜ ክልል የሚገኝ ወጣት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ አገራት መደበኛ የሰዎች ዝውውር እርስ በእርሳቸው እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል የተጣጣመ የፖሊሲ  ማዕቀፍ አላቸው ወይ? የሚለው ጉዳይ በፎረሙ ምክክር ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል በዋነኛነት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።

በውይይቱም አገራት ዜጎች ደህንነታቸውና መብታቸውን በጠበቀ መልኩ መስራት የሚያስችላቸው ወጥነት ያለው የአሰራርና የሕግ ማዕቀፍ ለመዘርጋት ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን አመልክተዋል።

በሌላ በኩል በምስራቅ አፍሪካና አፍሪካ ቀንድ አገራት አንድ ዜጋ ወደ ሌላ አገር ሄዶ ለመስራት የሚያስችለው ተመሳሳይ የትምህርትና የስልጠና ስርዓት እንደሌለ ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት።

ከዚህ አኳያም ኢትዮጵያ፣ኬኒያና ታንዛኒያ መካከል ተመሳሳይ የሆነ የትምህርትና የስልጠና ስርዓት በመዘርጋት ዜጎች በአገራቱ መካከል ተንቀሳቅሰው መስራት የሚያስችላቸው ፕሮጀክት መቅረጻቸውንና ይህም በፎረሙ ላይ በተሞክሮ መልክ መቅረቡን አመልክተዋል።

ሶስቱ አገራት የጀመሩትን ወጥነት ያለው ስርዓት የመዘርጋት እንቅስቃሴ በሌሎች አገራት ቢሰፋ የተሳለጠና ምቹ የሆነ መደበኛ የሰው ኃይል ዝውውር ለመፍጠር እንደሚያስችልም ነው ያስረዱት።

በተጨማሪም ከአባል አገራቱ የተወጣጡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ፎረሙ የሚመራባቸውን የተለያዩ ፖሊሲዎችና የሕግ ማዕቀፎች ማዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።

ማዕቀፎቹ ፎረሙ በዘላቂነት ተቋማዊ መልክ ይዞ እንዲቀጥል ለማድረግ የፋይናንስ ሀብት ማሰባሰብ አማራጮችን መያዛቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ፎረሙን በሊቀ መንበርነት  በመራችበት ያለፉት ሁለት ዓመታት በአባል አገራት መካከል የተጠናከረ የሰው ኃይል ልማት በመዘርጋት መደበኛ የሰዎች ዝውውርና ወጥነት ያለው የፍልሰተኞች  አስተዳደር እንዲኖር ሲሰራ መቆየቷንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች የሚኒስትሮች ፎረም ሊቀ መንበርነቷን ለዩጋንዳ በይፋ አስረክባለች።

የምስራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቀጣናዊ የፍልሰት ጉዳዮች የሚኒስትሮች ፎረም የተቋቋመው እ.አ.አ በ2020 በኬንያ ናይሮቢ በተካሄደ ስብሰባ ነው።

ፎረሙ አገራት  ለስራ ፍለጋ በሚንቀሳቀሱና በሚሰደዱ ዜጎች ላይ ባወጧቸው ፖሊሲዎች ላይ የጋራ መፍትሔ የሚያበጁበት፣የተሰላጠ የሰው ኃይል ዝውውር የመፍጠር እንዲሁም የስደተኞች የሰብዓዊ፣የስራ ቦታና ማህበራዊ መብቶቻቸው እንዲጠበቁ ለማድረግ የሚሰሩበት ማዕቀፍ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም