አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን- የማህበረሰብ ተወካዮች - ኢዜአ አማርኛ
አገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን- የማህበረሰብ ተወካዮች
ዲላ ፤ የካቲት 21 /2016 (ኢዜአ)፡- አገራዊ የምክክር መድረኩ ለአንድነትና ዘላቂ ሰላም መሠረት የመጣል ግቡን እንዲያሳካ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የጌዴኦ ዞን የማህበረሰብ ተወካዮች ገለጹ።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጌዴኦ ዞን ላለፉት ሶስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው በአገራዊ ምክክር የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮችን መረጣ አጠናቋል፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የማህበረሰብ ተወካዮች፤ የምክክር መድረኩ ለአገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መሠረት የመጣል ግቡን እንዲያሳካ የሚደግፉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተመራጮች መካከል የጌዴኦ ዞን አይነ ስውራን ማህበር ፕሬዚዳንት መምህር ተሰማ ወሬራ ፤አገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በውይይት ይፈታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።
ለዚህም ስኬት የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ምክክሩ ለአገራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መሠረት እንዲጥል የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት የዲላ ከተማ ንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሻለቃ አረጋኸኝ አሰፋ ናቸው።
መንግስት በአገሪቱ ሚስተዋሉ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በማሰብ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም የወሰደውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ምክክሩ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ በማበጀት አገርን ወደ እድገት ጎዳና ለማሻገር መሠረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለኮሚሽኑ ስራ ስኬታማነትም ተሳትፏቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የዲላ ከተማ ነዋሪ አቶ ፀጋዬ ታደሰ፤ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት ያለውን አካታችነት አጠናክሮ ሊያስቀጥል ይገባል ብለዋል።
በተለይም የባህል ተቋማት ለሰላም እሴት ግንባታ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ከተቋማቱ ጋር በትብብር መስራት ለምክክሩ ውጤታማነት ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን አስተያየት ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌጡ በበኩላቸው፤መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የውይይት መድረኩ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ የአጀንዳና የማህበረሰብ ተወካዮች ልየታ በተሳካ መልኩ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጌዴኦ ዞን ይህንኑ ተግባሩን ላለፉት ሶስት ቀናት ማከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም ከ 1 ሺህ 100 በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደተሳተፉና ከዘጠኝ ማህበራዊ መሰረቶች ከ350 በላይ ተወካዮች መመረጣቸው ተመልክቷል።