አድዋን የዘከሩ ስንኞች

2150

የታሪክ ድርሳናት የአድዋ ድልን በተለያየ መንገድ ዘክረውታል። ምሁራንም አንድምታውን በየዐውዱ ዘርዝረዋል። በዚህም ለሰው ልጆች በተለይም ለጥቁሮች አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እንደሆነ ደምድመዋል። በርግጥም የአድዋ ድል ታሪክም፣ ትርክትም የለወጠ ትልቅ ሁነት ነው። 

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ምዕራባዊያን 'አቢሲኒያ' በሚሏት ጥንታዊት አፍሪቃዊት ምድር የነበረው ክስተት ቀለምና ዘር ቀመስ በሆኑ በሰው ልጆች መካከል ድል መንሳትና መነሳት፣ ተስፋ እና ቀቢፀ ተስፋ፣ ሀሜትና ሀሞት፣ ብስራትና መርዶ... እያፈራረቀ አበሰረ። ለሀገሬው ዘመን-አይሽሬ አሻራ አነበረ። ውርስም ቅርስም ሆነ!!

ይህ ክስተት በታሪኩ ልክ በኪነ ጥበብ ተዘክሯል ባይባልም ቅሉ በጥበብ ፈርጁ ተወስቷል። የኪነ-ጥበብ ሰዎች በየመክሊቶቻቸው ድሉን ለመዘከር ጥረዋል። ሙዚቀኞች በዜማዎቻቸው፣ የሲኒማ ሰዎች እና ፀሐፈ ተውኔቶች በተውኔታቸው፣ ሊቃውንት በቅኔዎቻቸው አድዋን ዘክረዋል። ዕውቅ ገጣሚያን ደግሞ ቃላት እያዋደዱ፣ በዘይቤና ዘመን እያዋሃዱ፣ ምዕናብና ገሀድ እያዛነቁ፣ ታሪክና ትዝብት እያሰባረቁ ... አድዋን በግሩም ስንኞቻቸው ከትበውታል። በአድዋ ድል ምርጥ ግጥሞች መካከል "ጥቂት ስንኞች" እየመዘዝን በወፍ በረር ቅኝት እንመልከት። 

ባለቅኔው ፀጋዬ ገብረመድህን በ‘እሳት ወይ አበባ’ ግጥም መድብሉ አድዋን መልክዓ ምድራዊና ሃሳባዊ ወሰኗን አድማስ ተሻጋሪ፣ ሰማይ ታካኪ፣ ታሪካዊ ስፍራዋ የአጽም ርስትና የደም ትቢያ የተሸበለለባት መቀነት አድርጎ መስሏታል። በዚህች ታሪካዊ ስፍራ በተከፈለው መስዋዕትነት ከባርነትና ነጻነት ስርየትን ሲያጎናጽፍ፣ የኩራት ቅርስ መሆኗንም ሰፊውን ታሪክ በጥቂት ስንኞች እንዲህ ቋጥሯል። 

".... አድዋ ሩቅዋ፣ 

የዓለት ምሰሶ የአድማስ ጥግዋ፣

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ...

ዓድዋ የዘር አፅመ ርስትዋ- የደም ትቢያ መቀነትዋ

ከሞት ከባርነት ሥርየት- በደም ለነጻነት ስለት

አበው የተሰውብሽ እ’ለት

የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ- የኢትዮጵያዊነት ምስክርዋ..."

ገጣሚው አለፍ ሲልም በጦርነቱ የዋሉ መሳሪያዎችን፣ የጦር መሪዎችን እጅና ጓንትነት በፈረስ ስሞቻቸው በመቋጠር /ለአብነትም የዳግማዊ ምኒልክ፣ የራስ መኮንን፣ የደጃች ባልቻ ሳፎ፣ የፊታውራሪ ገበየሁና ሌሎችም/ ኢትዮጵያዊያንን ጀግንነትና ወኔ በአጭሩ ቋጥሮታል።

...ድው-እልም ሲል ጋሻዋ- ሲያስተጋባ ከበሮዋ፣

ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ፣

ያባ መቻል ያባ ዳኘው፤ ያባ ነፍሶ ያባ ቃኘው፣

ያባ ጎራው፣ ያባ በለው በለው ሲለው..." በሚል።

ደራሲና ጋዜጠኛ ነብይ መኮነን ‘ስውር ስፌት’ በተሰኘ የግጥም መድብሉ የአድዋን ድል ሲያመሰጥረው አድዋን ‘በደም ግብርነት’ ይገልጸዋል፤ ታሪኩንም ላጥፋህ ቢሉት የማይጠፋ ሕያው ቀንዲል አድርጎታል።

“አድዋ የደም ግብር ነው፤ አበው የለኮሱት ቀንዲል፣ 

አድዋ የአፍሪካ ዱካ ነው፤ አበሽ የከተበው ፊደል፣

ላጥፋህ ቢሉት መች ይጠፋል፤ ጠላት በልቶ ያፈራ ተክል፣ 

ለዛሬም ታሪክ ነው፣ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’  ለሚል...”

የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ምሁር ሰይፉ መታፈሪያ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) “የተስፋ እግር ብረት” መጽሐፍ “የድል በዓል ማለዳ” በሚል ርዕስ የአድዋን ድባብ ከማለዳው ምናባዊ ትዕይንት ጀምሮ ይቃኛል። ገጣሚው የሰንደቁን መውለብለብ፣ የሕብረ ቀለሙን ድምቀት ከልክ በላይ ውስጥን ኮርኩሮ የሚያስፈግግ ሐሴት እንዳለው በዘይቤያዊ ቃላት ገልፆታል። ገጣሚው በቅኔው የሠራዊቱን ቆራጥነት፣ በወኔ በደም ሲቅላላ፣ የመድፍ አረር ሲያፋጭ ይስለዋል። በስሜት ስካር አድዋ ደፍርሶ በስዕለ ህሊናው የነበረውን የጦርነቱ ማለዳዊ ድባብም እንዲህ ያብራራዋል።

ዐይነ-ልቦናዬ ዐጽም ያያል፤ የድል ሜዳውን ይቃኛል።

ባድዋ ድል በዓሉ ማለዳ፤ የበዓል መድፍ ሲንዱዋዱዋ

(ዱዋ ዱዋ ዱዋ ዱዋ!)

ከሞት እንቅልፍ ተቀስቅሶ፤ ያ-ዐጽም ዙርያውን ደባብሶ

ጉሮሮውን ጠረገ፣ እህህህህ! እህህህህ!... እያለ ይቀጥላል።

በአድዋ ኮረብታማ ተራሮች የተኙ ጀግኖችን በሕይወት ተኝተው የሚያንኮራፉ አስመስሎም አቅርቧቸዋል።

...ድንጋይ ተንተርሶ፤ አፈር ቅጠሉን ለብሶ፣

ከዚያን ያንኮራፋል፤

እንደዚሁም በቅብልብል

የወደቀበቱ ሜዳው፣ ተረተሩ፤ 

ቀን የማይለውጠው ምስክሩ

የዚያ ጀግና፣ የዚያ ኩሩ።

ገጣሚ አበረ አያሌው “ፍርድና ዕርድ” በተሰኘው የግጥም ስብስቡ ባሰፈራቸው ስንኞች ‘ነገረ አድዋ’ን ከመንደር ወደ አገር፣ ከአገር ወደ አህጉር በመጨረሻም ከአህጉር አተልቆ ‘ዓለም’ ያደርገዋል፤ አድዋን የአፍሪካ ብርሀን ፈንጣቂ፤ ለእብሪተኞች ደግሞ የትካዜና ቅስም መስበሪያ ምስጢር አድርጓታል። በተለይም ኢትዮጵያ ለገጠማት አሁናዊ የዘር ፖለቲካ አዙሪት አድዋን ለሚያሳንሱ ወገኖች በቅኔው ምላሽ ይሰጣል።

"...እነ ምኒልክ ጦር ይዘው ከመድፍ የተዋደቁ

ጎራዴ መዘው የሮጡ በጠብ-መንጃ አፍ ያለቁ

ለጓጉለት ነጻነት -ደማቸውን ያፈሰሱ

ለሰፈር ብቻ አይደለም- የአህጉር ድል አታሳንሱ።

...

ዓድዋ ሰፈር አይደለም - ዓድዋ መንደር አይደለም እሱ

ዓለም ናት ዓድዋ ቤቱ - ሃገር ናት የድል ትራሱ

ለጠበበ የዘር ቅኔ - የደም ድል አታሳንሱ!..." በማለት ገልጾታል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ምሁሩ ተሻገር ሽፈራው (ዶ/ር) ‘የነፍስ ርችቶች’ በተሰኘ የግጥም ስብስብ መፅሃፉ ከቋጠራቸው ስንኞች መካከል በአድዋ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል የግጥም ውድድር ያሸነፈበትን ረጅምና ድንቅ ግጥም አካቷል። የዶክተር ተሻገር ግጥም አንጓ እና ስንኞች የአድዋን ምጡቅነት፣ ዝና፣ ነቅዓ ፍትሕ፣ ውበትና ቅኔ በውብ ቃላት ገልጠውታል።

"... ዓድዋ አንቺ የዝና አጽናፍ

ሕዝቦች እፍ ያሉብሽ ቁጣ - የነበልባል እቶን ጫፍ

እጹብ ክስተት፤ ደቂቅ ረቂቅ፤ ምጡቅ ጠሊቅ

ኬላ ድንበር፣ አድማስ ሰበር፣ የቅርብ ሩቅ

ለትንግርትሽ ብቻ መጥኔ

ትንግርት እውነት፣ ታምር ሁነት፣

የብርቅ ብርቅ፣ የድንቅ ድንቅ

ለሰጠሽው ፍትህ መጠን - ለፍርድሽ ሚዛን ብያኔ

ለንግስትሽ ሥነ ውበት - ለታሪክሽ ምስጢር ቅኔ…"

ገጣሚው "... በምን ቀሰም፣ በምን ቀለም - በምን ብዕራና ሊከትበው..." ሲል የአፍሪካዊያን ሁሉን አቀፍ ድል ለመግለጽ የቀለም፣ የአንደበትና የብራና ወኔ እንዳጣባት ይናገራል። በመጨረሻም ይህችን የድል ቁንጮ የማትሞቺ ህያው ጀንበር ሁልጊዜም ተዘመሪ፤ ተወደሽ" ይላታል።

"… እና ዓድዋ አንቺ በኩር የድል መኸር

የቅኝ ግዛት ቀንበር ሰንሰለቱ እንዲሰበር

ተጠቂዎች አጥናፍ አጥናፍ የመረጡሽ የትግል ዘር

ህይወት ከፍለው እልፍ - ያርጉሽ የመረጡሽ ከአገር አገር

የማታልፊ የማትከስሚ - የማትሞቺ ህያው ጀንበር

ሰብዓዊ ድል ነሽና - ስምሽ ይወደስ ይዘመር…"

   (በአየለ ያረጋል)

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም