ቀጥታ፡

የአድዋ ድል በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ ታላቅነቱን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር በጸጥታ ዙሪያ በቂ ዝግጅት ተደርጓል 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ ታላቅነቱን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር በጸጥታ ዙሪያ በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለጸ።

128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ በደማቅ ሁኔታ ይከበራል።

የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል ታሪኩን በሚመጥንና የሰራዊቱን አኩሪ ገድል በሚያጎላ መልኩ የሚከበር መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።

በዓሉ በማዕከል ደረጃ በቅርቡ በተመረቀው የአድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑም ተገልጿል።

የበዓሉን አከባበር በተመለከተ በተለይም በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ የተደረገውን ዝግጅት በሚመለከት ኢዜአ የአዲስ አበባ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሚዴቅሳ ከበደ ጋር ቆይታ አድርጓል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው በማብራሪያቸው የአድዋ ድል በዓል ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ ታላቅነቱን በሚመጥን መልኩ እንዲከበር በጸጥታ ዙሪያ በቂ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።

በዓሉን በሰላም ለማክበር ከሰላም ሰራዊቱና ከህዝባዊ ኃይሉ፣ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና አጠቃላይ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የአድዋ ድል በዓል አከባበርን በማስመልከት በሁሉም የመዲናዋ አካባቢዎች ለአንድ ሳምንት ያህል ህዝባዊ የፓናል ውይይቶች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡

በፓናል ውይይቶችም የአድዋ ድልን በተመለከተ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን የማጠቃለያ ፕሮግራሙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በዛሬው እለት ተካሒዷል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ለማክበር እንዲሁም በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ እንደ ሰላም ሰራዊትና ህዝባዊ ኃይል ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም አቅጣጫ በመትመም የጠላት ሃይልን ድል በመንሳት ታሪክ የሰሩበት የአድዋ ድል አሁን ላይ ከታሪክነቱ ባለፈ የህብረ-ብሄራዊነትና የአንድነታችን መገለጫ ሆኗል።

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያም ባለፈ የመላ የጥቁር ህዝቦች ታላቅ የድል ብስራት፤ የአንድነት ምልክትና የጀግንነት መገለጫ መሆኑም ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም