ቀጥታ፡

የአድዋ ንግሥተ ሳባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸው ተማሪዎች አስመረቀ

አክሱም፣ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፡ - በትግራይ ክልል   የሚገኘው የአድዋ ንግሥተ ሳባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በ12 የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 360 ተማሪዎች አስመረቀ።

የኮሌጁ ዲን መምህር ተስፋ ዘርዑ እንዳሉት ኮሌጁ  ዛሬ ያስመረቃቸው ሰልጣኞች በደረጃ  አራት የተሰጠውን ስልጠና የተከታተሉ ናቸው።

ከተመራቂዎቹ መካከል 170 ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ተመራቂዎቹ ከሰለጠኑባቸው መስኮች መካከል ኮምፒዩተር ሳይንስ፣ አካውንቲንግ፣ አውቶ መካኒክ፣ በእንጨት ሥራና ኮንስትራክሽን ይገኙባቸዋል።

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የትምህርት፣ ስልጠና፣ የሰራ እድል ፈጠራ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ገነት አረፈ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳስገነዘቡት ተመራቂዎች የመንግስትን ሥራ  ሳይጠብቁ ሥራ በመፍጠር ህይወታቸውን መምራት አለባቸው።

የአድዋ ንግሥተ ሰባ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ከዚህ በፊት በተለያዩ ሙያዎች እያሰለጠነ የገበያ ከፍተት ሲሞሉ ከቆዩ ኮሌጆች መካከል አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም የመንግሥት ሥራ  ሳይጠብቁ፤ በራሳቸው ሥራ  በመፍጠር ሞዴል እንዲሆኑ ሃላፊዋ አሳስበዋል።

የአድዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ዮሐንስ ገብረ አምላክ ባደረጉት ንግግር ተመራቂዎች የሰለጠኑበትን ሙያ ወደ ተግባር መቀየር አለባቸው ያሉ ሲሆን የከተማው አስተዳደርም ተመራቂዎቹ ሥራ  እንዲፈጥሩና ብድር በማመቻቸት እገዛ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

በደረጃ 4 አውቶ መካኒክ ሙያ የተመረቀው ገብረ ጻድቃን ገብረ ሃዋርያ፣ በሰለጠነበት ሙያ  ከሌሎች ጋር ተደራጅቶ ለመሥራት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

በኮንስትራክሽን ዘርፍ በደረጃ 4 የተመረቀው ወጣት ጎይቶኦም አብርሃም በሰለጠነበት ሙያ ሕዝብና አገሩን ለማገልገል መዘጋጀቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም