የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት ነው-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት ነው-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይ ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ሥራ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።
አውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ብሔራዊ ጥቅሟን አስከብራ ለመዝለቅ ያደረገችውን ጉዞ እና ዲፕሎማሲያዊ ከፍታዋን ያሳየ መሆኑንም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፤ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም አውደ-ርዕዩ ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በሳይንስ ሙዚየም መከፈቱን አስታውሰዋል።
ዓላማውም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከጥንት እስካሁን ያለውን ተግዳሮት እና ከፍታ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ ማስረዳት መሆኑን ገልጸዋል።
መጪውን ዲፕሎማሲ ዘመኑን በዋጀ አዲስ የአስተሳሰብ ቅኝት በመቅረጽ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን አስከብራ ለመዝለቅ የሚያስችላትን ፍኖተ-ካርታ ማመላከት ከዓላማዎቹ መካከል ይገኙበታል ብለዋል።
አውደ-ርዕዩ ለ48 ቀናት መቆየቱን ጠቅሰው፤ ከ250 ሺህ በላይ በሆኑ ዜጎች መጎብኘቱንም ጠቁመዋል።
በዚህም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የከተማ እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ከውጭ ሀገራት ደግሞ ኤምባሲዎች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከ116 ዓመት በላይ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ታሪካዊ እጥፋቶችን የሚያስቃኝ የመጀመሪያ ቅጽ መጽሐፍ ከአውደ-ርዕዩ ጎን ለጎን መመረቁን ተናግረዋል።
አውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማሳየት የተቻለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ሥራ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ሥራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በድኅረ-ለውጥ ወቅት የገጠማትን የውስጥ እና የውጭ ጫና ለመመከት ያደረገችው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እና ከፍታዎችን ማሳየት መቻሉን ጠቁመዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ በብዙ ወጀቦች መሀል ሆና ከዋናው ሀገራዊ ግብ ሳትደናቀፍ ብሔራዊ ጥቅሟን እና ክብሯን ማስከበር መቻሏን ጠቁመዋል።
የውጭ ሀገራት ዜጎች እና ተቋማት እንዲሁም ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የዲፕሎማሲ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን በድጋሚ ለማረጋገጥ መቻላቸውንም ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ-ርዕይ "ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" በሚል መሪ ቃል መካሄዱ ይታወሳል፡፡