ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ የአየር ትንበያ መረጃ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመስጠት ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው

ጅማ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ትንበያ መረጃ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመስጠት ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ በጅማ ከተማ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው የምዕራብ ኦሮሚያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር ማዕከል ተመርቋል።


 

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ የአየር ጸባይ መረጃን ሰብስቦ በመስጠት ህይወትና ንብረትን ከአደጋ የመጠበቅ ስራ እያከናወነ ነው ።

ኢንስቲትዩቱ በተለይም ለግብርናው ዘርፍ ልማት አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ገልጸው፣ በአቪዬሽን ሚቲዎሮሎጂና  በሌሎችም ዘርፎች ድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ተቋሙ የሚሰበስባቸውን የአየር ትንበያ መረጃዎች ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብም ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም አቶ ፈጠነ አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አስተማማኝ መረጃ ለመስጠት በጅማ፣ በጅግጅጋ፣ በሐዋሳ፣ በባህር ዳርና በጋምቤላ ከተሞች  ማዕከላት እንዳሉት ገልጸዋል።

ጅማና አካባቢው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው የግብርና ልማት የሚታወቅ በመሆኑ የግብርና ልማትን የአየር ጸባይ ትንበያ መሠረት ባደረገ አገልግሎት ለማጎልበት ጥረት እንደሚደረግ ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አማካሪው አቶ ሞቱማ መቃሳ የአየር ጸባይ ለውጥ ዓለምን እየፈተነ ያለ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፣በአየር ጸባይ ለውጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቋቋም አንደኛው መንገድ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ መስጠት እንደሆነ አመልክተዋል። 


 

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የሚሰጠውን መረጃ መጠቀም ጎርፍና ድርቅን የመሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ለመከላከል ዓይነተኛ አስተዋጽኦ  እንዳላቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የምእራብ ኦሮሚያ ሚቲዎሮሎጂ ምርምር ማዕከል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ገመቹ ራጋ ማዕከሉ  በአካባቢው ግብርናና ኢንዱስትሪ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማበርከት እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

ሰባት ጣቢያዎችን የሚያስተዳድረው ማዕከል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅትና በጋራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ለማዕከሉ የሚያገለግለው ህንጻ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ ግንባታው መጠናቀቁ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል።

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችም ማዕከሉን ጎብኝተዋል ።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም