ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የተከተለ የምርት ጥራትና አገልግሎት ቁጥጥር እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስታንዳርድን የተከተሉ የምርት ጥራትና አገልግሎት ቁጥጥር  እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት ገለጸ።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 13 ሺህ በምርት ጥራት የፍተሻ ላብራቶሪ፣ በወጪና ገቢ ምርት ኢንስፔክሽንና ሰርቲፊኬሽን የጥራት ማረጋገጫ መስጠቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት የኮሙኒኬሽንና ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ተክኤ ብርሃነ፤ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የፍተሻ፣ የቁጥጥርና የዕውቅና ማረጋገጫ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በዚሁ አሰራር መሰረት በተቋሙ ጅቡቲን ጨምሮ በአዲስ አበባ እና በክልል ዘጠኝ ቅርንጫፎች ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር ጥራት ያለው አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ድርጅቱ ከ12 መንግሥታዊ ተቋማት ጋር በምርት ጥራትና አገልግሎት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ሲያደርግ መንግሥታዊና ላልሆኑ ተቋማትም ስልጠና መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በምርት ጥራትና አገልግሎት፣ በተስማሚነት ምዘና፣ በቴክኖሎጂና ሌሎችም ዘርፎች መድረኮችን በማመቻቸት ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ወራት 13 ሺህ በምርት ጥራት የፍተሻ ላብራቶሪ፣ በወጪና ገቢ ምርት ኢንስፔክሽንና ሰርቲፊኬሽን የጥራት ማረጋገጫ ተሰጥቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የላብራቶሪ ፍተሻ፣ ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን፣ የአሰራር ስርዓቶችን በመተግበር ለላኪዎች፣ አምራቾች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ ለደንብ አስፈጻሚ አካላት፣ ለሸማቾች እና አጠቃላይ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም