" የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ " መጽሐፍ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
" የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ " መጽሐፍ ተመረቀ

አዲስ አበባ ፤የካቲት 21/2016 (ኢዜአ) ፦ " የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ " መጽሐፍ ተመረቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከአዲስ ዋልታ እንዲሁም የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በጋራ ያዘጋጁት ይህ መጽሐፍ ስድስት ምዕራፎች አሉት።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃፋር በድሩ፤ ኢትዮጵያ በውኃ ሀብት ብትታደልም በበቂ ሁኔታ አልተጠቀመችም ብለዋል።
የሁለት ውኃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ ለኢትዮጵያ ነባራዊ ፍላጐት መፍትሄ የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል።
መጻኢ ዕድልን ለመወሰን ፈተናን ለመሻገር ትልቅ ፋይዳ ያለው መጽሐፍ መሆኑን ጠቁመው ኢትዮጵያ ባላት የውሃ ሃብት ልክ ተጠቃሚ መሆን አለባት ብለዋል።
ሁለት ውኃዎች ተብለው በመጽሃፉ የተጠቀሱት የዓባይ ወንዝ እና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ጂኦ-ፖለቲካ፣ ብሔራዊ ደኅንነት በመወሰን ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም አብራርተዋል።
መጽሐፉ ኢትዮጵያ በተፋሰሱ የውኃ ተጠቃሚነት ላይ ጉልህ ሚና መጫወት እንደሚገባት የሚዳስስ፣ የህግና የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያነሳና የባህር በር ለማግኘት የተደረገው የትግል ጉዞ ከታሪክ አንጻር በስፋት እንደሚዘረዝርም ጠቅሰዋል።
የተመረቀው " የሁለት ውሃዎች ዐቢይ ስትራቴጂ " መጽሐፍ ለሀገር ሕልውና ተግዳሮት የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ታስቦ ከበርካታ ጉዳዮች አንጻር የተቃኘ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአዲስ ዋልታ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መሃመድ ሀሰን በበኩላቸው፤ ትውልዱ ስለሁለቱ ውሃዎች እንዲያውቅ ፣ እንዲማርና እንዲመራመር መጽሐፉ ስትራቴጂካዊ መንገዶችን ያመላክታል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ እና በቀይ ባሕር ላይ ያላትን አቋም የሚያንፀባርቅ የፖሊሲ ሰነድ በመፅሀፍ መልኩ ተዘጋጅቶ መቅረቡም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
መጽሐፉ የዓባይ ተፋሰስ እና የባህር በር ጉዳይ ዐቢይ ስትራቴጂ አዲስ ዕይታ፣ በዓባይ ተፋሰስ የውሃ ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና መጫወት፣ የሕግና ፖሊሲ ጉዳዮች በዓባይ ውሃ አጠቃቀም፣ ስለ ባሕር በር የዓለም አቀፍ ሕግ እና የሃገራት ተሞክሮ እና የባሕር በር ለማግኘት የተካሄደ ትግል እንዲሁም ጥቅሞቻችን ልንከተላቸው የሚገቡ መርሖችና ስትራቴጂዎች በሚሉ ስድስት ምዕራፎችን የተዘጋጀ ነው።
መጽሐፉ በታሪክ፣ በፖለቲካ በሳይንስና በሌሎችም ዘርፎች ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ምሁራን ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንም ተጠቁሟል።
በአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት በተካሄደው የምረቃ መርሃ ግብር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሃብታሙ ኢተፋ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የመከላከያ ተወካዮች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።