የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ዛሬ በድሬዳዋ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ውድድር ዛሬ በድሬዳዋ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤የካቲት 21 / 2016 (ኢዜአ)፡- የ2016 አ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር መርሐ ግብር ዛሬ በ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በድሬዳዋ ስታዲየም ጅማሮውን ያገኛል።
የፊፋን ደረጃ ባሟላ መልኩ እድሳቱ የተጠናቀቀው የድሬዳዋ ስታዲየም የፕሪሚየር ሊጉን የሁለተኛ ዙር ጨዋታ እንዲያስተናግዱ ከተመረጡት ሶስት ስታዲየሞች አንዱ ነው፡፡
በዚህም ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ በመጀመሪያ ዙር ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች በስድስቱ ሲያሸንፍ በአምስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
የጣና ሞገዶቹ ባለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በአራቱ ተሸንፈዋል።
በአጠቃላይ በ15 ጨዋታዎች 22 ነጥብ በመያዝ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አምና በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ባህር ዳር ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጥሩ ግስጋሴ እያደረገ አይገኝም።
በአንጻሩ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ መድን በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። ሰባት ጊዜ ተሸንፎ ስድስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
መድን ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። በሁለቱ ሲሸነፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።
በውጤት ማጣት ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በ12 ነጥብ 13 ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሌላኛው የ16ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከሀምበሪቾ ዱራሜ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በመጀመሪያ ዙር በሊጉ ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች አምስቱን ሲያሸንፍ በስድስቱ ተሸንፏል። አራት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይቷል።
ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በአንዱ ሽንፈት አስተናግዷል። በሁለቱ ነጥብ ተጋርቷል።
በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በአንጻሩ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው ሀምበሪቾ ዱራሜ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 15 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በ10ሩ ሲሸነፍ በአራቱ አቻ ወጥቷል።
በአሰልጣኝ መላኩ ከበደ የሚመራው ሀምበሪቾ ዱራሜ በሰባት ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።
የ16ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል የሊጉ መሪ መቻል ከሀዲያ ሆሳዕና ከቀኑ 10 ሰዓት፤ ፋሲል ከነማ ከሀዋሳ ከተማ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የ16ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ የካቲት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።
የ2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ውድድር በድሬዳዋ ፣ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና አዲስ አበባ ስታዲየሞች እንደሚከናወን የፕሪሚየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታውቋል።