ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጣቶች እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ትምህርት ሞጁል ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብሔራዊ የወጣቶች እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ትምህርት ሞጁል መርሃ -ግብር ይፋ አደረገ።

ባንኩ የማስተማሪያ ሞጁሉን ያዘጋጀው "ከፈርስት ኮንሰልትና ከማስተር ካርድ ፍውንዴሽን" ጋር በመተባበር መሆኑም ተገልጿል፡፡

የማስተማሪያ ሞጁሉ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የፋይናንስ ክህሎት በማጎልበት የፍይናንስ አካታችነት ለማሳደግ የሚረዳ ነው።

የወጣቶችን እና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በክህሎት ላይ የተመሰረተ የፋይናንስ አጠቃቀምን በማሳደግ የተሻለና ዘላቂነት ያለው የስራ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ያግዛል።

የማስተማሪያ ሞጁሉ በመላ አገሪቱ በፋይናንስ ተቋማት፣ በመንግሥትና በልማት አጋር ድርጅቶች በተናጠል እየተከናወነ ያለውን የፍይናንስ ትምህርት ወጥነት፣ ቀጣይነትና በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

ይህ የፋይናንስ ማስተማሪያ ሞጁል ቁጠባ፣ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፣ ብድር፣ ኢንሹራንስ፣ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት፣ የበጀት አዘገጃጀትና ሌሎች የፋይናንስ አገልግሎቶችን የሚሸፍን ሲሆን ለሴቶች የስራ ፈጣሪዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገኙ ሲሆን ሞጁሉ የፍይናንስ አጠቃላይና አስተዳደር ላይ ያለባቸውን የክህሎት ክፍተት ለመሙላት ትኩረት በማድረግ የተዘጋጀ ነው ተብሏል።

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አማካሪ ማርታ ሀይለማሪያም ባንኩ የኢትዮጵያ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚዎችን የግንዛቤ ደረጃ በማሳደግ የፋይናንስ አካታችነትና የዘርፍን ጤናማነት ለመጨመር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የሆነው ሞጁልም እንደ አሮፓውያን አቆጣጠር በ2025 የፋይናንስ አገልግሎት ላይ ግንዛቤ ያላቸውን ወጣቶችና የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ 75 በመቶ ለማድረስ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም