ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ55 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባው ዘመናዊ የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የካርጎ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በ55 ሚሊዮን ዶላር ያስገነባው የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ተመርቋል።

በመረሃ -ግብሩ ላይ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር በለጠ ሞላ፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው፣ የአየር መንገዱ የቦርድ አባላት፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እንዲሁም የካርጎ ተጠቃሚ ዓለም አቀፍ አስመጪና ላኪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል ዘመናዊ አሰራሮችን መተግበሩን ቀጥሏል ብለዋል።

በዓለም ላይ የዲጂታል ግብይት እያደገ በመምጣቱ የመደበኛው ካርጎ አገልግሎት እየቀነሰ በአንጻሩ የኢ-ኮሜርስ የካርጎ አገልግሎት እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው ለዚህም አየር መንገዱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።

 

ለዚህም የካርጎ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያ በ55 ሚሊየን ዶላር በ15 ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ሦስተኛውንና ለኢ-ኮሜርስ (በኦን ላይን የሚገዙ እቃዎችን) የሚውል ዘመናዊ የካርጎ ማዕከል ማስገንባቱን ገልፀዋል።

በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓት የሚገዙ እቃዎችን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በአዲስ አበባ በኩል ለማጓጓዝና የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

የካርጎ ማዕከሉ የተለመደ አገልግሎት የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ዓለም እየሄደበት ያለውን አዲስ የገበያ ስልት ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ያለው መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል።

የተገነባው የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአህጉራዊ ምጣኔ ሃብት መሳለጥና የነፃ ንግድ ቀጣና ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአጠቃላይ ገቢው ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሰበሰበው ከካርጎ አገልግሎት መሆኑን በመጥቀስ የዘርፉን አቅም ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎት ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው በጀት ዓመት ካስገባው አጠቃላይ 6 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ገቢ 2 ቢሊየን ዶላር የሚሆነው በካርጎና ሎጂስቲክ አገልግሎት ያስገባው ነው።

በቅርቡም የ2023 ምርጥ የካርጎና ሎጅስቲክስ ኦፕሬተርና የአፍሪካ ምርጡ የካርጎ ኦፕሬተር በሚል አየር መንገዱ በሁለት ዘርፎች ለአምስተኛ ጊዜ መሸለሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው የኢ-ኮሜርስ ማዕከል ግንባታው በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ በቅርቡ ለኢዜአ መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም