ቀጥታ፡

ቀደምት አባቶች በአድዋ ያስመዘገቡትን ድል የአሁኑ ትውልድ በኢኮኖሚ መድገም አለበት-ምሁራን

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦ ቀደምት አባቶች በአድዋ ያስመዘገቡትን ድል የአሁኑ ትውልድ በኢኮኖሚው መድገም አለበት ሲሉ የታሪክ ተመራማሪ ምሁራን ገለጹ።

የአሁኑ ትውልድ የአድዋን ድል ሲያከብር አንድነትንና አብሮነትን በማጠናከር ለአገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም እድገት ኃላፊነቱን እየተወጣ ሊሆን  ይገባልም ብለዋል።

የታሪክና የባህል ተመራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘከሪያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተደማጭነት በማጉላት ረገድ የአድዋ ድል ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

አድዋ ለጥቁር ህዝቦች ነጻነትና እኩልነት መንገድ የከፈተና ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስከበረ አኩሪ ታሪክ ነው ብለዋል።

ቀደምት ጀግኖች አባቶቻችን የአገራቸውን ሉአላዊነትና የህዝቦችን ነጻነት አሳልፎ ላለመስጠት በከፈሉት መስዋትነት የዛሬዋን ኢትዮጵያ እውን ማድረግ ችለዋል።

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ አገርን ለማጽናትና ጠብቆ ለማቆየት ከተከፈለበት የአድዋ ድል በመማር የተሻለች ኢትዮጵያን መፍጠር ይጠበቅበታል ነው ያሉት።

ለዚህም ትውልዱ ጠባቂ ሳይሆን በእውቀቱ፣ በጉልበቱና በአቅሙ መስራትና መለወጥን የሚያልም በመሆን በአገሪቱ እየተከናወነ ላለው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የድርሻውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆን አለበት።

በዋናነት የዚህ ዘመን ትውልድ ከቀደምት ጀግኖች በአድዋ ድል የተረከባትን ታሪካዊት አገር ለማስቀጠል ድህነትን በማጥፋት የራሱን አሻራ ለማኖር ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አየለ በክሪ በበኩላቸው የአድዋ ድል በወቅቱ ለተመዘገበው ስኬት ብቻ ሳይሆን ለዚህ ዘመን ትውልድም ትልቅ ምሳሌ የሚሆን ነው።


 

በመሆኑም ይህንን ድል ወደ ሃብት በመቀየር ሒደት ውስጥ አድዋ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገለጸው፤ ይህንን መጠቀምና ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ። 

የአድዋ ድል አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ይረገጡበት የነበረውን የግፍ ስርአት ታግሎ በማሸነፍ ለመላ ጥቁር ህዝቦችን ነፃነት ያወጀ ታላቅ ታሪካዊ ሁነት ነው።

128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ይከበራል።

የአድዋ ድልን ታሪካዊ ዳራ መነሻ አድርጐ የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያም የኢትዮጵያ ጀግኖችንና የአድዋ መልክዓ ምድርን በሚገልፅና እሴቱን ጠብቆ ለእይታ ክፍት መሆኑ ይታወቃል።

ይህም የአድዋ ድልን በሚመጥን መልኩ ለመዘከርና ታሪኩን ለትውልዱ ለማስተላለፍ በእጅጉ የሚያግዝ ያደርገዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም