ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይን ከ250 ሺህ በላይ  ዜጎች ጎብኝተውታል- አምባሳደር ብርቱካን አያኖ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርእይ ከ 250 ሺህ በላይ በሆኑ ዜጎች መጎብኘቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም አውደ ርዕዩ ጥር 2 ቀን 2016 በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሳይንስ ሙዚየም መከፈቱን አስታውሰዋል።

አውደ ርዕዩ ለ48 ቀናት መቆየቱን ጠቅሰው፤ ከ250 ሺህ በላይ በሆኑ ዜጎች መጎብኘቱንም ጠቁመዋል።

አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማሳየት የተቻለበት መሆኑን ተናግረዋል።


 

አውደ ርዕዩ ያለፉት 116 ዓመታት ጉዞ ማስቃኘት የተቻለበት እና ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያሳረፈቻቸውን አሻራ ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።

እንዲሁም ዲፕሎማሲው አሁን ላይ ያለበት ደረጃን እና ቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በተመለከተ አቅጣጫ የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

 ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ስራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ለአውደ ርዕዩ ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ "ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን" በሚል መሪ ቃል መካሄዱ ይታወሳል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም