ለፓን-አፍሪካዊነት ማበብ ትልቅ አበርክቶ የነበረው የኢትዮ-ጋና ግንኙነት ከፖለቲካ ባሻገር በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮችም ሊጠናከር ይገባል- ጋናዊ ምሁር ዶክተር አህመድ ቡግሪ - ኢዜአ አማርኛ
ለፓን-አፍሪካዊነት ማበብ ትልቅ አበርክቶ የነበረው የኢትዮ-ጋና ግንኙነት ከፖለቲካ ባሻገር በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮችም ሊጠናከር ይገባል- ጋናዊ ምሁር ዶክተር አህመድ ቡግሪ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 21/20216 (ኢዜአ)፦ ለፓን-አፍሪካዊነት ማበብ ትልቅ አበርክቶ የነበረው የኢትዮ-ጋና ግንኙነት ከፖለቲካ ባሻገር በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስኮችም ሊጠናከር እንደሚገባው በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የሕግ አማካሪው ዶክተር አህመድ ቡግሪ ገለጹ።
በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ የሆኑት ጋናዊ ዶክተር አህመድ ቡግሪ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ኢትዮጵያ የጥቁሮች ብቻ ሳትሆን የሰው ዘር መገኛና የነጻነት ትዕምርት ናት።
ጋና ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ከባርነት ቀንበር የተላቀቀች የጥቁሮች አብሪ ኮከብ እንደሆነች ገልፀው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ጋናን ጨምሮ ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ንቅናቄ ሁነኛ ምልክት ሆና ማገልገሏን ገልጸዋል።
ሁለቱ ለፓን አፍሪካዊነት ማበብ ትልቅ አበርክቶ የነበራቸው ሀገራት እንደሆኑ ገልፀው፤ ኢትዮጵያን ይህን ዕድል ለትውልድ ግንባታ መጠቀምና ለአፍሪካዊያን ማዕከልነቷን ማጽናት አለባት ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ፖለቲካዊ ትስስር የነበራቸው እና የሁለቱ ሀገራት ህዝቦችም የሚያመሳስላቸው ታሪክና ስነ ልቦና ያላቸው እንደሆኑ ያነሳሉ።
በመሆኑም የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣናን እና ሚሊዮኖችን ባስተሳሰረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ ዕድል በመጠቀም የሁለትዮሽ የህዝብ ለህዝብ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ማጎልበት እንደሚገባቸው ነው ያነሱት።
የፓን አፍሪካዊነት ፅንሰ ሃሳብ አፍሪካ በአፍሪካዊያን የተገባች ትሆን ዘንድ በቀደሙት አባቶች የተጀመረው እና የዛሬው አፍሪካዊ ትውልድም ሊመራበት የሚገባው እሳቤ እንደሆነ ዶክተር አህመድ ይናገራሉ።
የጋና ነጻነት መሪና የነጻይቱ ሀገር መሪ ፕሬዝዳንት ንክዋሚ ንኩርማ፣ ቀዳማዊ አፄ ኅይለሥላሴና ሌሎች ቀደምት መሪዎች አንድ የተባበረች አፍሪካዊ መንግስት የመገንባት ህልምና ነበራቸው ይላሉ።
ይህን የፓን አፍሪካዊነት እሳቤ ቀጣዩ ትውልድ በቅኝ ግዛት ልቦና ውቅር ተጽዕኖ በመውደቁ ለመከፋፈል እና ለተናጠላዊ ሉዓላዊነት ትኩረት እንዳደረገው አስረድተዋል።
አፍሪካዊያን የተሟላ ሉዓላዊነት የሚኖራቸው በተሳሰረችና አንድነቷ በተጠበቀ አፍሪካ ጥላ ስር እንጂ በተናጠል አካሄድ ባለመሆኑ ከ60 ዓመታት በኋላም ወጣቱ ትውልድ ሊያቀነቅነው እንደሚገባ አንስተዋል።
የዚህ ዓመት ትምህርት ዓመት መሆኑ አፍሪካዊያን የሚበጀውን ትስስር ላይ በማተኮር ዘመኑን የሚመጥን ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አላቸው።
የአፍሪካዊያን ትምህርት ከቅኝ ግዛትና ባርነት ትርክት ባሻገር ከአውሮፓዊያን ስርዓተ ትምህርት የተፋታ የራሳ ባህል፣ ታሪክ እና ፓን አፍሪካዊነት መልክ ባለው ትምህርት ትውልድ መቅረጽ እንደሚገባ ተናግረዋል።
አፍሪካ ሕብረት የቀድሞ መሪዎችን ሐውልት ማቆሙ ፓን አፍሪካዊነትን ለዚህ ትውልድ ለማስተማር እና ህልማቸውን ለማጋባት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
ከዶክተር ንኩዋሚ ንኩርማ ጀምሮ በቀዳማዊ አፄ ኅይለሥለሴ እና ዘንድሮ ደግሞ ለጁሊዬስ ኔሬሬ በተለያዩ አቅጣጫዎች መታሰቢያ ሐውልት መሰራቱም አንዱ ትውልድን በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለማነጽ አጋዥ መሳሪያ ነው ብለዋል።