ኦቪድ ግሩፕ 5 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሸጥ የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኦቪድ ግሩፕ 5 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሸጥ የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2016 (ኢዜአ) ፦ኦቪድ ግሩፕ 5 ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሸጥ የሚያስችለውን ስምምነት አደረገ።
ኦቪድ ግሩፕ በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አልሚነት ከሚያስገነባቸው 60 ሺህ ቤቶች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ 5 ሺህ ቤቶችን ለመሸጥ የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት አድርጓል::
በመርኃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የኦቪድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዮናስ ታደሰ እና የሁለቱ ተቋማት የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል::
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አየር መንገዱ ከ17 ሺህ በላይ ሰራተኞች እንዳሉት በመግለጽ ተቋሙ የሰራተኞቹን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረዋል::
በዚህም አየር መንገዱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ሰራተኞቹ መኖሪያ ቤት የሚያገኙበትን ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡
ነገር ግን የሰራተኞቹ የቤት ፍላጎት ሰፊ በመሆኑ ከኦቪድ ግሩፕ ጋር መግባቢያ ስምምነት መፈፀሙን ገልፀዋል::
የኦቪድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ በበኩላቸው በመንግስትና የግሉ ዘርፍ አልሚነት ኦቪድ ግሩፕ ለመገንባት ካቀዳቸው 60 ሺህ ቤቶች ውስጥ 5 ሺ ቤቶችን ለአየር መንገዱ በታቀደለት የጊዜ ገደብ ገንብቶ እንደሚያስረክብ ገልፀዋል::