ቀጥታ፡

በቅርንጫፉ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል

ዲላ፤ የካቲት 20/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በግማሽ በጀት ዓመቱ  ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና ወጪ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዙን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ በኮንትሮባንድ ቁጥጥር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራአስኪያ አቶ ታደሰ መርድ በወቅቱ  እንዳሉት የኮንትሮባንድ ንግድ አሁንም በማህበራዊና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል።

ባለፉት ስድስት ወራት ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ያሳተፈ ጠንካራ ሥራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

በጽህፈት ቤቱ ስር በሚገኙ ሰባት የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በተደረገ ቁጥጥር ከ1 ቢሊዮን 50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸውን አስረድተዋል።

ከተያዙት እቃዎች መካከል መድኃኒት፣ ልባሽ ጨርቅና ጫማ እንዲሁም የኤሌክትሮንክስ እቃዎች ዋንኞቹ እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

አቶ ታደሰ እንዳሉት በቁጥጥር ስር ከዋሉት እቃዎች መካከል 990 ሚሊዮን ብር የሚገመተው የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች ናቸው።

ከዓምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ610 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቁመው፣ "ይህም የኮንትሮባንድ ፍሰቱ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል" ብለዋል።

የኮንትሮባንድ ፍሰቱን ለመግታት ኮሚሽኑ ከ1 ሺህ በላይ አዲስ የሰለጠነ ባለሙያን የመመደብ፣ የአመራር ለውጥ የማድረግ እና የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ማከናወኑንም አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

ይህም ከህብረተሰብ ተሳትፎ መጎልበትና ቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ጋር ተዳምሮ ለውጤት ማብቃቱን ተናግረዋል።


 

የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር በተደረገው ጥረት ህብረተሰቡን ጨምሮ የባለድርሻ አካላት ድርሻ የጎላ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በሀዋሳ ቅርንጫፍ የጪጩ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስተባባሪ ኮማንደር ቅባቱ መራኒ ናቸው።

"በጣቢያው ባለፉት ስድስት ወራት ህገወጥ መድኃኒትን ጨምሮ መሰል ህብረተሰቡን በቀጥታ የሚጎዱ እቃዎች ወደሀገር ውስጥ ሊገቡ ሲሉ በህብረተሰብ ጥቆማ ተይዘዋል" ብለዋል።

በጣቢያው በፍተሻ፣ በክትትልና ጥቆማ ከ247 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባን እቃ መያዙንና ይህም በጣቢያው ታሪክ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልዴ በበኩላቸው የኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከርና ወጥ አቋም መያዝ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድ በአካባቢ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የኮንትሮባንድ ዝውውር ለመቆጣጠር በተቀናጀና በተደራጀ አግባብ የሚሰራው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።

በተለይ በህገወጥ አዘዋዋሪዎችና ተባባሪዎች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ ከኮሚሽኑና ከጌዴኦ ዞን የተውጣጡ የሥራ ሃላፊዎች፣ የጸጥታ አካላት እና የዞኑ የጸረ ኮንትሮባንድ ግብር ሃይል አባላት ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም