የአድዋ ድል የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ፣ የድል ምልክትና የኩራታችን መገለጫ ነው - አፍሪካዊያን ጋዜጠኞች - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ፣ የድል ምልክትና የኩራታችን መገለጫ ነው - አፍሪካዊያን ጋዜጠኞች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ፣ የድል ምልክትና የኩራታችን መገለጫ ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጋዜጠኞች ገለጹ።
የአድዋ ድል አፍሪካውያን በነጮች የበላይነት በቅኝ ግዛት ይረገጡበት የነበረውን የግፍ ስርአት ታግሎ በማሸነፍ ለመላ ጥቁር ህዝቦች ነፃነትን ያወጀ ታላቅ ታሪካዊ ሁነት ነው።
ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለቅኝ ገዥዎች አንበረከክም በማለት በዱር በገደሉ ተዋግተው በማሸነፍ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ፋና ወጊ መሆንም ችለዋል።
በዚህም አድዋ አፍሪካዊያን በትግላቸው ነፃነታቸውን እንዲያረጋግጡ የድል አድራጊነት መነሻ በመሆን የመላ ጥቁር ህዝቦች የድል ተምሳሌት ተደርጎም ይወሰዳል።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የኢትዮጵያ ጀግኖች ለነፃነታቸው ተዋግተው ያሸነፉበት ታሪካዊ እለት ሆኖ እየተከበረ እስካሁንም ዘልቋል።
የአድዋን ድል በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋና፣ ኒጀርና ሴኔጋል ጋዜጠኞች የአድዋ ድል የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ፣ የድል ምልክትና የኩራታችን መገለጫ ነው ብለዋል።
በጋና ጆይ ኒውስ ቲቪ የውጭ ጉዳዮች ዘጋቢ ጋዜጠኛ ብለስድ ሶጋህ፤ የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የጀግንነት ማሳያና የአህጉሪቷ የነፃነት ብስራት መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም የአድዋ ድልን የጥንካሬና የይቻላል ስነ-ልቦና በመሰነቅ የሁላችንም ችግር የሆነውን ድህነት በጋራ መዋጋት አለብን ብሏል።
የኒጀሯ ጋዜጠኛ፣ የፊልም ዳይሬክተርና ኤዲተር ራህማቱ ኬይታ፤ የአድዋ ድል የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት አርማ፣ የድል ምልክትና የኩራታችን መገለጫ ነው ብላለች።
የአድዋ ድል የቅኝ ግዛትንና ጭቆናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሸነፍ ያስቻለ፤ የመላ አፍሪካውያን የድል ተምሳሌት ስለመሆኑም አንስታለች።
ሴኔጋላዊው ጋዜጠኛ የአፍሪካ 24 ሚዲያ ማናጀር አሊ ጉይንዶ፤ የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን በጀግንነት ታሪክ የሰሩበት የሁላችንም የጋራ ታሪክና የነፃነታችን አርማ ነው ብሏል።
የጋና ጆይ ኒውስ ቲቪ የውጭ ጉዳዮች ዘጋቢ ጋዜጠኛ ብለስድ ሶጋህ፤ የአፍሪካን አንድነት እውን በማድረግና ለነፃነት ግንባር ቀደም ትግል በማድረግ የኢትዮጵያ ሚና በታሪክ ሲወሳ የሚኖር መሆኑን ገልፃል።
ኢትዮጵያ አሁንም የአፍሪካን አንድነት፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ ፓን አፍሪካ ሚዲያ መፍጠር ያስፈልጋል የሚል አቋም ይዛ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።