ኢትዮጵያ ለደን ልማት የሰጠችው ትኩረት ከካርቦን ሽያጭ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለደን ልማት የሰጠችው ትኩረት ከካርቦን ሽያጭ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር አድርጓል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለደን ልማት የሰጠችው ትኩረት ከካርቦን ሽያጭ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር ማድረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ የደን ልማት ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን የ13 በመቶ ድርሻ እንዳለው በቅርቡ የተደረገ አገር አቀፍ ጥናት ያመለክታል።
ደንና እጽዋት ላይ የተመሰረተ ልማት የአካባቢ መራቆትን ለመከላከል፣ የግድቦችን ውሃ የመያዝ አቅም ለመጨመርና ለመስኖ ስራ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ትልቅ ድርሻ አለው፡፡
ከዚህ ባለፈ ከደን ልማት የሚገኘው ጥቅም ለአገሪቷ ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የደን ልማት ከፍተኛ ባለሙያዎች ተመናምኖ የነበረውን የደን ሽፋን ለማሳደግ በተደረጉ ጥረቶች አሁን ላይ የደን ሽፋኑ 17 በመቶ መድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
በተለይም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ለአገሪቷ ደን ሽፋን መጨመር፣ለብዝሃ ህይወት መበራከትና የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ የደን ልማት ከራሷ አልፎ አለም እየተፈተነበት ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መፍትሄ እየሰጠ መሆኑን ነው ባለሙያዎቹ የገለጹት።
አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ የደን ልማት ዕውቅና ከመስጠት ባለፈ በተጨባጭ ለተገኘው ውጤት የሚከፍለው ክፍያ እየጨመረ መምጣቱንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ባለሙያና የአገር አቀፉ አረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) እንደሚሉት የደን ልማት ለስነምህዳር መሻሻል ካለው ጠቀሜታ ባለፈ አገሪቷ ከካርቦን ሽያጭ ገቢ እንድታገኝ አስችሏታል።
አገራት የኢትዮጵያን የደን ልማት ስራዎች በተጨባጭ በመፈተሽ ተገቢውን ክፍያ እየፈጸሙ መሆኑንም ነው ያነሱት።
በኢትዮጵያ ደን ልማት ብሔራዊ የ”ሬድ ፕላስ” ፕሮግራም አስተባባሪ ይተብቱ ሞገስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከደን ልማት ብቻ በአመት ግማሽ ቢሊዮን ዶላር የማግኘት ዕድል እንዳላት ነው ያነሱት።
ያደጉት አገራት ለአየር ብክለት ያላቸው ድርሻ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ለማካካስ በታዳጊ አገራት ደን በማልማት የካርቦንዳይኦክሳይድ ጋዝን ከከባቢ አየር ለመቀነስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን በመሸፈንና ደን በማልማት ወደ ከባቢ አየር የሚገባን የተበከለ አየር በመቀነስ ሃላፊነቷን በአግባቡ እየተወጣች መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ከካርቦን ሽያጭ የሚገኘው ክፍያ ለተጨማሪ የደን ልማትና አካባቢ ጥበቃ ስራዎች የሚውል መሆኑንም ነው ባለሙያዎቹ ያነሱት።
የካርበን ሽያጭ ክፍያ ደንን ከጭፍጨፋ በመከላከልና በማልማት የካርበን ልቀትን በመቀነስ ለሚከናወነው ሥራ የሚከፈል ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ደን ልማት ዕውቅና ከሰጡ አጋር አገራት ኖርዌይ አንዷ ናት።
ኖርዌይ ኢትዮጵያ በደን ልማት ዘርፉ እያከናወነች ላለው ስራ የ75 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ለመፈጸም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት መፈረሟ ይታወሳል።