ቀጥታ፡

በፅንፈኛ ቡድኑ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ሻለቃ ግርማ ሃይለማርያም

ሰቆጣ፤የካቲት 20 ቀን 2016 (ኢዜአ) ፡- በአማራ ክልል የህዝቡን ወግ፣ ባህልና እሴት ለማጥፋት እየሞከረ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል  በሰሜን ምስራቅ ዕዝ የ101ኛ ኮር 65ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥ ሻለቃ ግርማ ሃይለማርያም ገለጹ።

የተሃድሶ ስልጠና ላጠናቀቁና  በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ለተመደቡ ለቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት በሰቆጣ ከተማ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በሰሜን ምስራቅ ዕዝ የ101ኛ ኮር 65ኛ ክፍለ ጦር ምክትል አዛዥና የብሄረሰብ አስተዳደሩ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሻለቃ ግርማ ሃይለማርያም በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ የቀድሞው የልዩ ሃይል አባላት በሰሜኑ ጦርነት ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ መስዋዕትነት ከፍለዋል።

አሁን ላይም የክልሉን ህዝብ ወግ፣ ባህልና እሴት ለማጥፋት እየሞከረ ያለውን ፅንፈኛው ቡድን በመታገል የበኩላቸውን ሚና እንደሚጫወቱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

በዚሁ ፅንፈኛው ቡድን ላይ  የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። 

የህዝብን እንቅስቃሴ በመገደብ፣ ጥሪቱን በመዝረፍና መሪን በመግደል የአማራ ህዝብ ወኪል ነኝ ማለት የክህደት ማሳያ ጥግ ነው ብለዋል። 

አርሶ አደሩ ማዳበሪያ እንዳያገኝ በመከልከልና ንብረቱን በመዝረፍ ችግር ውስጥ መከተት ተገቢነት እንደሌለው ያመለከቱት  ሻለቃ ግርማ ፤ ይሄን ቡድን  መታገል የሁላችንም ድርሻ መሆን አለበት ብለዋል።


 

በዚህም ስልጠና ወስደው የተመደቡ የቀድሞ የልዩ ሃይል አባላት ከመከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የክልሉ የጸጥታ ሃይሎች ጎን ተሰልፈው በመታገል ህዝባዊነታቸውን እንዲያረጋግጡም መልዕክት አስተላልፈዋል። 

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሉ ግርማይ በበኩላቸው ፤ለሀገር ሰላምና ሉዓላዊነት መጠበቅ የአካባቢው ህዝብ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ለኢትዮጵያ ዘብ የቆመ መሆኑን ተናግረዋል። 

የብሄረሰብ አስተዳደሩን ብሎም የክልሉን  ሰላምና ደህንነት አደጋ የጣሉትን ከመከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የክልሉ የፀጥታ ሃይሎች ጎን በመሰለፍ መስዕዋትነት እየከፈለ የሚገኝ ህዝብ ነው ብለዋል።

መንግስት ቅድሚያ ለሰላም በመስጠት ጥሪ ማቅረቡን ያወሱት አቶ ሃይሉ ፤ በአስተዳደሩ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ችግር ውስጥ የገባውን ቡድን  ወደ ሰላም በማምጣት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። 

የቀረበላቸውን የሰላም ጥሪ የማይቀበሉትን ለመታገል በሚደረገው ጥረት የተሃድሶ ስልጠናውን ያጠናቀቁ የቀድሞው የልዩ ሃይል አባላት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

ከዚህ ቀደም ሲልም የተሰጣቸውን የተሀድሶ ስልጠና ላጠናቀቁ የቀድሞ  ልዩ ኃይል አባላት  በደሴ ከተማና በደቡብ ወሎ ዞን ተመሳሳይ አቀባበል መደረጉን በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም