ቀጥታ፡

የአንድነትና የማሸነፍ ጥንካሬንና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ከአሁኑ ትውልድ ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅብናል - ዶክተር ድሪባ ኢቲቻ

ጋምቤላ፤የካቲት 20 / 2016(ኢዜአ) በዓድዋ ድል የታየውን የአንድነትና የማሸነፍ ጥንካሬንና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ከአሁኑ ትውልድ ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅብናል ሲሉ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ድሪባ ኢቲቻ ገለጹ። 

128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል የተመለከተ የውይይት መድረክ ‹‹ዓድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ›› በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል። 

የዩኒቨርሲቲዉፕሬዚዳንት በዚሁ ወቅት እንዳሉት የዓድዋ ድል የቀደሙ አባቶቻችን ለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ሲሉ በጀግንነትና በጋራ ዋጋ በመክፈል የኢትዮጵያን ነፃነት ለትውልድ ያሸጋገሩበት ታሪካዊ ዕለት ነው ብለዋል። 

የዓድዋ ድል የዓድዋል ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች "የነፃነትና የድል አድራጊነት ተምሳሌት ነው" ያሉት ዶክተር ድሪባ፤ ድሉም አባቶች በጋራ መስዋዕትነትና እልህ አስጨራሽ ትግል ያጎናጸፉን ታሪካዊ አርማ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በዓድዋ ድል የታየውን የአንድነትና የማሸነፍ ጥንካሬንና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ከአሁኑ ትውልድ ከፍተኛ ኃላፊነት ይጠበቅብናል ብለዋል።


 

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የሀገሪቱን እድገት የሚያፋጥኑ ብቁ ዜጎችን ከማፍራት ጎን ለጎን የምርምር ስራዎችን በማከናወን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በማቃለል ረገድ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ዶክትር ድሪባ ተናግረዋል። 

የሀገሪቱን ገናና ታሪክ ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የጋራ የሆኑ ትርክቶች ላይ አተኩሮ መስራት ይጠይቃል ያሉት ደግሞ የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፓል ፖዝ ናቸው፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች በቋንቋ፣ በቀለምና በሃይማኖት ሳይለያዩ በጋራ ታግለው ለትውልዱ ያወረሱት አንጸባራቂና ታሪካዊ አርማ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ብዙነህ ምክሩ እንዳሉት ለግጭት ምክንያት እየሆኑ ያሉትን የተዛቡ ትርክቶችን በማስተካከል "የቀደምት አባቶችን የዓድዋ የወል ታሪክ ለትውልዱ ማውረስ ይገባል" ብለዋል።

በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትን በብቃት የሚረዱ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

"ሀገራዊ አንድነታችንን በማጎልበት የውጭ ጣልቃ ገብነትን በጋራ ልንከላከል ይገባል" ያሉት ደግሞ ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ሞገስ አበበ ናቸው።

‹‹ዓድዋን ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ›› በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደውን የውይይት መድረክ ያዘጋጁት የሰላም ሚኒስቴርና ጋምቤላ ዩኒቨርስቲ በጋራ በመሆን ነው፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም