የአድዋ ድል ውርሶች በተለያዩ ባለሙያዎች አንደበት - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል ውርሶች በተለያዩ ባለሙያዎች አንደበት
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል ውርሶች በተለያዩ ባለሙያዎች አንደበት ።
የአድዋ ድል ከታሪካዊ ሁነቱ ባሻገር ለትናንት እስከ ነገ የሚዘልቅ ትምህርትነቱ፣ ውርሶቹ እና መልኮች በበይነ ዲሲፕሊነሪ ገጽታዎች ይላበሳል።
ይሄውም በታሪክ ሊቃውንት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ሙያዎች ውስጥ ያሉ ምሁራን የራሳቸው ዕይታ የሚሰጡበት፣ ዜጎችም እሴቱን የወረሱበት እና እንደ ማህበረሰብ የልቦና ውቅር የተነበረበት ድል ነው።
ለአብነትም የአድዋ ድል ካወረሳቸው ለኢትዮጵያዊያን እሴቶች መካከል የሀገር ፍቅር፣ መስዋትነትና ጀግንነት ሲሆን ከአድዋ ድል በኋላ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ ወረራዎችን ለመቀልበስ እርሾ ሆነዋል።
የሥነ ሕይዎት ተመራማሪዎች የሰው ልጆች ከተፈጥሮ እና ከአካባቢ ተለምዶ ማንነታቸው እንደሚቀረጽ ያትታሉ።
ዕውቁ የሥነ ሕይወት ሊቅ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላም የአድዋ ድል መሰል የአባቶች ታሪኮች የልጆችን ማንነትና ስለ ሀገር ያላቸውን ዕሳቤ እንደሚቀርጽ ገልጸዋል።
እርሳቸውም የአስተዳደጋቸው ሂደት ማንነታቸውን እንደቀረጸ ገልፀው፤ የአደዋ ድልም ከተበዱሉ ጎን መቆም፣ የሰው ልጆችን ማክበር እንዲሁም የራስን ነጻነት ማስከበርን እንደሚያስተምር አብራርተዋል፡፡
አድዋ ድል የመላው ጥቁሮች ብቻ ሳይሆን ነጻነትን እና ክብርን ላለማስደፈር የተደረገ የሰው ልጅ ተጋድሎ ውጤት መሆኑን ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተቃርኖ እሳቤዎቸን በማቀራረብ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በስፋት የሚንቀሳቀሱት አቶ ንጉሡ አክሊሉ በበኩላቸው አድዋን ለዛሬ ሀገራዊ ችግሮችን የምንሻገርበት ትልቅ ትምህርት ይሰጣል ይላሉ።
ይሄውም የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ችግሮችን በጋራ ሆኖ መቀልበስ የቻለበት በመሆኑ አሁናዊ ሀገራዊ ፖለቲካዊ ችግሮችን በጋራ ውይይት መፍታት እንደሚገባ ልንማርበት እንደሚገባ ነው ያነሱት።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን ቅድመ አያቶቻቸው በትብብር አድዋ ላይ ያስመዘገቡትን ድል በመማር አሁንም ግጭት፣ እርስ በርስ ጦርነት እና ቅራኔን ፈትተው ወደ ሀገራዊ መግባባት ሊመጡ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
ለዚህም የጋራ ዓላማ ይዞ በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር እንደሚገባ ነው ያነሱት።
የአድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ ለዚህ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸው፤ አደዋ ለመላው ጥቁር ሀዝቦች የነጻነት ትምህርት በመሆኑ ኤምባሲዎች ይህን እድል በመጠቀም እያስተዋወቁ መሆኑን ገልጸዋል።