ቀጥታ፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ድሉን በዓመት አንዴ ከማክበር ባለፈ በተሟላ መልኩ ድሉን ዘወትር ለመዘከር እድል ይፈጥራል-  የታሪክ ተመራማሪው አየለ በክሪ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ድሉን በዓመት አንዴ ከማክበር ባለፈ በተሟላ መልኩ ድሉን ዘወትር ለመዘከር እድል ይፈጥራል ሲሉ  የታሪክ ተመራማሪው አየለ በክሪ ገለጹ። 

የአድዋ ድልን ታሪካዊ ዳራ መነሻ አድርጐ የተገነባው አድዋ መታሰቢያ  ሙዚየም የኢትዮጵያ ጀግኖችንና የአድዋ መልክዓ ምድርን በሚገልፅ መልኩ ታሪካዊ እሴቱን ጠብቆ ተገንብቷል።

ሙዚየሙ በከተማችን ውስጥ እስከዛሬ ከተገነቡ እና በመገንባት ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ግዙፉ ሲሆን 11 ብሎኮችን የያዘ 45 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው።

የመታሰቢያ ሙዚየሙ የአድዋ ድል ታሪክ በትውልዶች መካከል ተጠብቆ እንደሚቆይ የሚያስችል መሆኑን ነው የታሪክ ተመራማሪው የገለጹት ።

የታሪክ ተመራማሪው አየለ በክሪ የአድዋን ድል በየዓመቱ ከማክበር ባለፈ የድሉን ታሪክ የሚመጥኑና ተጋድሎውን ተጨባጭ በሆነ መንገድ ለማሳየት የሚያስችሉ ቦታዎች እንዳልነበሩ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መገንባት ድሉን በዓመት አንዴ ከማክበር ባለፈ በተሟላ መልኩ ድሉን ዘወትር ለመዘከር እድል ይፈጥራል ብለዋል።

መታሰቢያው ኢትዮጵያውያን ለአንድ ዓላማ በጋራ በመቆም በአድዋ ያሳኩት ዘመን ተሻጋሪና አኩሪ ገድል በቋሚነት እንዲወሳ መንገድ የሚከፍት ነው ብለዋል።

  የአድዋ ድል መላው ጥቁር ህዝቦች ቅኝ አገዛዝን አምርረው እንዲታገሉ ወኔ ያስታጠቀ በመሆኑ ታሪኩን ለትውልድ ከማስተላለፍ አንጻር የመታሰቢያው መገንባት ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል። 

ኢትዮጵያዊያን በጋራ በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን የአድዋ ድል የሚዘክር መታሰቢያ መገንባቱ መጪው ትውልድ የአባቶቹን ጀግነት እንዲወርስ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

የአድዋ ድል በዘመናት ሂደት ተጠብቆ እንዲቆይና ትውልዱን ከታሪኩና ከባህሉ ጋር ከማስተሳስር አንጻር ሙዚየሙ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው አመልክተዋል። 

የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) መመረቁ ይታወቃል።

128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም  ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም