የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነትና ህብረት የታየበት አኩሪ ገድል ነው- አርቲስቶች - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነትና ህብረት የታየበት አኩሪ ገድል ነው- አርቲስቶች
አዳማ፤ የካቲት 20 /2016(ኢዜአ)፡- የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች ትብብር፣አንድነትና ህብረት የታየበት አኩሪ ገድል መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው አርቲስቶች ገለጹ።
አርቲስቶቹ እንዳሉት፤ አድዋ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሌም የሚኮራበት ነው፤ ለዚህ ድል ቋሚ ሙታሰቢያ መገንባቱ ድሉን የሚመጥ ነው።
የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች ህዝቦችን በሚያሰባስቡ፣ በጋራ ማንነት ላይ በመመስረት የአገር ፍቅርና አንድነት በሚያጎሉ ትርክቶች ላይ መስራት አለብን ሲሉም ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አርቲስት ሙሀመድ አህመድ ቆቤ ፤ አድዋ የሁሉም ጥቁር ህዝቦች ድል ከመሆኑም ባለፈ ለአፍሪካ ብርሃን ያመጣ ታሪካዊ ገድል መሆኑን ተናግሯል።
አድዋ የአፍሪካ የድል ችቦ የተቀጣጠለበትና የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት የተጣለበት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች ትብብር፣አንድነትና ህብረት የታየበት መሆኑን ገልጿል።
የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች ህዝቦችን በሚያሰባስቡና በጋራ ማንነት ላይ በመመስረት የአገር ፍቅርና አንድነት በሚያጎሉ ትርክቶች ላይ መስራት አለብን ብሏል።
ቀደምት አባቶቻችን ለአሁኑ ትውልድ ጀግንነት፣ህብረትና አንድነትን አውርሰዋል ያለው አርቲስቱ፤ የአሁኑ ትውልድ ሰላምን፣ልማት፣አንድነትና እድገትን በማስቀጠል ለነገ ትውልድ የምትሆን አገር መገንባት አለበት ሲል መልዕክት አስተላልፏል።
የአድዋ መታሰቢያ ከመሪዎች ሚና ባለፈ የህዝቦች የጋራ ማንነትና አንድነት ውጤትና ተሳትፎን ጎልቶ ያሳየ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ኮሜዲያን አሰፋ ተገኝ ነው።
የአድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች የነፃነት አሻራ ያረፈበት ቢሆንም ይህንን የሚዘክር ቋሚ ምልክት አልነበረም ያለው ኮሜዲያን አሰፋ ፤ የመታሰቢያው መገንባት ለዚህ ምላሽ የሰጠ መሆኑንም ተናግሯል።
የተደበቀውን የአባቶች ታሪክ ይፋ ያወጣ ከመሆኑም ባለፈ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ መዘክር ነው ሲልም አክሏል።
የኦሮሚያ ፊልምና ኪነ ጥበብ ማህበር አባል አርቲስት ጌታሁን አብዲሳ በበኩሉ፤ በአድዋ ዙሪያ የነበረው የተሳሳተ ትርክት በተገነባው ቋሚ መታሰቢያ በማስተካከል የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህብረትና አሻራ ያረፈበት እንደሆነ በግልጽ መንጸባረቁን ገልጿል።
አድዋን ስንዘክር የነበረው በወረቀት በተፃፈ ታሪክና በየዓመቱ ቀኑን ጠብቀን ነው ያለው አርቲስት ጌታሁን ፤ ኢትዮጵያውያን ሳይከፋፈሉ በአንድነት የተጎናጸፉት አኩሪ ድል መሆኑን ተናግሯል።
ትውልዱ ከአድዋ አንድነት፣ፍቅርና ህብረትን በመማር ድሉን በልማትና እድገት ለመድገም በትብብር መስራት አለብን ብሏል።
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች ትብብር፣አንድነትና ህብረት የታየበት አኩሪ ገድል መሆኑን በተገነባው መታሰቢያ በሚገባ መንጸባረቁን አርቲስቶቹ በሰጡት አስተያየት አብራርተዋል።