የሙዚቃ ጥበብ ከአድዋ ድል እስከ ታሪክ ዘካሪነት ትልቅ ሚና አበርክቷል- ዳዊት ይፍሩ - ኢዜአ አማርኛ
የሙዚቃ ጥበብ ከአድዋ ድል እስከ ታሪክ ዘካሪነት ትልቅ ሚና አበርክቷል- ዳዊት ይፍሩ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2016(ኢዜአ)፦ የሙዚቃ ጥበብ ከአድዋ ድል እስከ ታሪክ ዘካሪነት ትልቅ ሚና ማበርከቱን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ማህበራት ሕብረት ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ ገለጸ።
በታሪካዊ ገጾች በደማቅ ቀለም የተጻፈው የአድዋ ጦርነት ሀገሬው ከየአቅጣጫው ያለ ልዩነት ጠመንጃና ጦር አንግቶ፣ ጎራዴ ታጥቆ ለሀገሩ ዘምቷል።
በአድዋ ጦርነት ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል በየፊናው ተሰማርቶ የራሱን ሚና እንደተጫወተ ሁሉ የጥበብ ሰዎችም ለድሉ መገኘት የራሳቸው ታሪካዊ አበርክቶ አድርገዋል።
በታሪክ የሚታወቁም ሆኑ በታሪክ ማንነታቸው ያልታወቁ የአድዋ ዘመን አዝማሪዎች ማሲንቋቸው ከድምጸታቸው ተዋህዶ ሰራዊቱን አነቃቅተዋል ዘማቹን አጀግነዋል።
ከዚህም ባሻገርም በዘመኑ የተገጠሙ ግጥሞቻቸው ዛሬም አድዋ በዓይነ ህሊና በምዕናብ እንዲሳል፣ የአድዋ ጀግኖች እንዲወሱ፣ የአድዋ ገድል እንዲዘከር በማድረግ ትልቅ ባለውለታዎች እንደሆኑ ይነሳል።
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘርፍ ማህበራት ሕብረት ፕሬዝዳንት ዳዊት ይፍሩ ለኢዜአ እንደተናገረው፣ የአድዋ የድል ብስራት ሁሉም ኪነ ጥበብ ሰዎች ሊያከብሩትና ሊዘክሩት የሚገባ ድል ነው።
የአድዋ ድል ሲዘከር የዘመኑ የሽለላ እና ፉካራ ክዋኔዎች፣ ድርሰትና ሌሎች የኪነ ጥበብ ስራዎች ሁሉ መታሰብ እንዳለባቸው ያነሳል።
በአድዋ ጦርነት ሰራዊቱን ወኔ በመቀስቀስ አዝማሪዎች የነበራትን ሚና በማውሳት፤ ለታላቁ ድል አድዋ መገኘት ሙዚቃ አይተኬ ሚና እንደነበራት ተናግሯል።
ሙዚቃ የአድዋን መንፈስ በትውልድ አዕምሮ ለማስረጽ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሶ፤ ይህም ለጋራ ትውልድ ግንባታም አይተኬ ሚና እንዳለው ያነሳል።
የሙዚቃ ጥበብ ከአድዋ ድል መገኘት እስከ ታሪክ ዘካሪነት ትልቅ ሚና እንደነበረው ጠቁሞ፣ የሙዚቃ፣ ሲኒማ እና ሌሎች የኪነ ጥበብ መስኮች ከአድዋ ታሪክ ጋር የተቆራኙ እንደሆኑም እንዲሁ።
ኪነ -ጥበብ ታሪክን ለትውልድ በመዘከር ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላት የሚያነሳው ዳዊት ይፍሩ፣ ሙዚቃን ጨምሮ ሁሉም የኪነ ጥበብ ዘርፎች አድዋን በቅጡ መግለጥና ለትውልድ ማሻገር እንደለባቸው ገልጿል።
የአድዋን መታሰቢያ ከሕንፃ ባሸገርም በኪነ ጥበብ መስክም በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቅሷል።