ቀጥታ፡

የትምህርት ተቋማት በስፖርት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2016(ኢዜአ)፦ የትምህርት ተቋማት በስፖርት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊው  ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ  የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተናገሩ።   

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስሩ ባሉት ኮሌጆች ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓም የስፖርት ፌስቲቫል እንደሚያካሂድ አስታውቋል።

በፌስቲቫሉ ማብሰሪያ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

በስፖርት ፌስቲቫሉ ላይ በዩኒቨርሲቲው ስር የሚገኙ ኮሌጆች የሚሳተፉ ሲሆን ውድድሩ እግር ኳስ ፣ ሩጫ ፣ ቅርጫት ኳስን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርቶችን ያካተተ ነው ተብሏል።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ኮሌጆች የምድብ ድልድል ዕጣ አወጣጥ ስነ ስርዓት በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ አማካኝነት ወጥቷል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ፤ስፖርት ኢኮኖሚን ለማሳደግ  ፣የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዲሁም ከአገራት ጋር ወዳጅነትን ለማጠናከር የላቀ ሚና አለው።

የአገርን ስም የሚያስጠሩ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ተከታታይነት ያለው ስራ ማከናወን እንደሚገባ ጠቁመው፣ ለዚህም ትምህርት ቤቶች ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የስፖርት ፌስቲቫል ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የተያዘው አገራዊ ጥረት እውን እንዲሆን አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች በስፖርት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ሁላችንም ከትምህርት ቤት ተነስተን ለዚህ ደረጃ የበቃን በመሆኑ ትምህርት ቤቶች ለስፖርት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል ብላለች።


 

ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይደረግ የነበረው ስፖርታዊ ውድድር መቋረጡን በማስታወስ ውድድሩ ቀጣይነት እንዲኖረው መስራት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥታለች።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው የስፖርት ፌስቲቫሉን ለማካሄድ የሚያስፈልጉ አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። 


 

የስፖርት ፌስቲቫሉ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ማደስ ፣ ደረጃ ማሻሻልና አዳዲስ ግንባታ ማከናወን ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም