ቀጥታ፡

በአፋር ክልል በበጀት ዓመቱ 161 ሺህ አባወራና እማወራዎች የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገለጸ

ሠመራ፤ የካቲት 19 /2016(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል በተያዘው የበጀት ዓመት 161 ሺህ አባወራና እማወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ  እንደሚሆኑ ተገለጸ። 

የክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የ2015 የስራ ዘመን ዕቅድ አፈፃፀምና የ2016 የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሠመራ ከተማ ተካሄዷል። 


 

የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን   አገልግሎት የተጀመረው በ2011 ዓ.ም ነው። 

በክልሉ አይሳኢታና አፋምቦ ወረዳዎች  የተጀመረው አገልግሎቱ  ወደ 15 ወረዳዎች በማሳደግ እስካለፈው  ዓመት ድረስ 70ሺህ የቤተሰብ አባላት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

ዓላማው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ  እንደሆነ አመልክተዋል።

ይህንንም የተሳካ ለማድረግ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አባላት ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። 

በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ዋና አስኪያጅ ዶክተር ኢድሪስ መሐመድ  በበኩላቸው፤ በተያዘው የበጀት ዓመት አገልግሎቱን በሌሎች  15 ወረዳዎች ተደራሽ  ለማድረግ መታቀዱን ተናግረዋል።

በዚህም  161 ሺህ አባወራና  እማወራዎችን ተጠቃሚ  እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ያምሮት አንዷለም ፤ በአገር  አቀፍ ደረጃ እየየተገበረ ያለው የጤና መድህን ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት እንደ የክልሎቹ ነባራዊ ሁኔታ ያጤነ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም   ክልሎች ባላቸው   መመሪያ መሠረት ተግባራዊ የሚያደርጉበት አግባብ መኖሩን ጠቁመዋል።

በአፋር ክልል በከፍተኛ አመራር አባላት  ደረጃ ትኩረት ያገኘ መሆኑን ተናግረዋል።

የብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል  ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኢሴ አደን፤  ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ እየተደረገ ያለው ጥረት  አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

በውጤታማነት ለማስቀጠል ስራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በመድረኩ ከክልሉ  ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም