ቀጥታ፡

ኖርዌይ ኢትዮጵያ በደን ልማት እያከናወነች ላለው ስራ የ75 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች

 አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2016(ኢዜአ)፦  ኖርዌይ ኢትዮጵያ በደን ልማት እያከናወነች ላለው ስራ የ75 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገች።

ድጋፉ ደንን በዘላቂነት በማልማት ወደ ከባቢ አየር የሚገባውን በካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ እያከናወነች ያለውን ስራ ለማበረታታት የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴና የኖርዌይ የአየር ንብረትና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር አንድሪያስ ኤሪክሰን ተፈራርመዋል።

የድጋፍ ስምምነቱ ኢትዮጵያ በደን ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እያከናወነች ያለውን ስራ አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ  ሁለቱ አገራት በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑን አስታውሰው፣ በተለይም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እያከናወነችው ላለው ስራ የኖርዌይ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

በአስር ዓመት የልማት እቅድ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተከናወኑ ከሚገኙ ተግባራት ውስጥ የደን ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ችግኞችን ከመትከል ባለፈ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን መጠቀምን የሚያበረታታ ፖሊሲ አውጥታ ተግባራዊ እያደረገች መሆኑንም ነው ያነሱት።

ደንን በዘላቂነት በማልማት የአየር ንብረት ለውጥን ተጽዕኖ ለመቀነስ የተከናወኑ ስራዎች ውጤታማ ለመሆናቸው ከኖርዌይ የተገኘው ድጋፍ ማሳያ መሆኑን  ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።

የኖርዌይ የአየር ንብረትና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር አንድሪያስ ኤሪክሰን በበኩላቸው ኖርዌይ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምትከተለውን የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ እንደምታደንቅ ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባትና የአየር ንብረት አሉታዊ ተጽዕኖን ለመቀነስ ተነሳሽነቱን ወስዳ መስራቷ ሊያስመሰግናት ይገባል ብለዋል።

ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች በጋራ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማምጣትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በደን ልማት ላይ እያከናወነችው ያለውን ስራ እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ በደን ልማት ላይ እያከናወነችው ያለው ስራ አሁን ካለው የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ለዚህ ደግሞ አገራቸው ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ደንንና የተራቆቱ አካባቢዎችን በዘላቂነት ለማልማትና ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የሚውል መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም