ቀጥታ፡

የንግድ ኩባንያዎች የብድር መመለስ ብቃት ምዘና አገልግሎት ሀገር በቀል  ኩባንያዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2016(ኢዜአ)፦ በንግድ ኩባንያዎች ላይ የሚደረግ የብድር የመመለስ ብቃት ምዘና አገልግሎት የሀገር በቀል ኩባንያዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማጎልበት የሚያስችል መሆኑን የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለጸ። 

የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በብድር የመመለስ ብቃት ምዘና እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከንግዱ ማህበረሰብና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የምክር ቤቱ ዋና ፀሀፊ ሺበሺ ቤተማርያም፤ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ የራሱን አሻራ እያሳረፈ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ ከንግዱ ማህበረሰብ ፈታኝ ጉዳዮች አንዱ የሆነው የካፒታል እጥረት ጉዳይ እንዲቀረፍ በትኩረት መስራቱን አስታውሰው፣ የካፒታል ገበያ መልሶ እንዲቋቋም ያደረገውን ጥረትም ጠቅሰዋል።


 

የንግድ ኩባንያዎች ካፒታል አቅርቦት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ከዓለም አቀፉ ብድር የመመለስ ብቃት ምዘና ኤጀንሲ በጋራ ለመስራት ከአንድ ወር በፊት ስምምነት መፈራረሙን ገልጸዋል።

ይህም የንግድ ኩባንያዎች በብድር የመመለስ ብቃት ምዘና ሂደት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የብድር አቅርቦት እንዲያገኙና የብድር አመላለስ ብቃታቸው እንዲጎለብት ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል።

የንግድ ኩባንያዎች በብድር የመመለስ ብቃት ምዘና አገልግሎት ማለፋቸው ሀገር በቀል ኩባንያዎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሻሻል እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት። 


 

የጎህ ቤቶች ባንክ ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰር እስክንድር ዲበኩሉ፤ የብድር መመለስ ብቃት ምዘና ባንኮች የብድር አዋጭነትን ለማረጋገጥና የብድር ክምችትን በየዘርፉ መደልደል ያስችላል ብለዋል።

በጥቅሉ የብድር መመለስ ብቃት ምዘና በአበዳሪውና ተበዳሪው ኩባንያ መካከል ሙሉ መተማመን ለመፍጠር እና የስጋት ትንተናን በቀላሉ ለመወሰን ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ፤ የብድር የመመለስ ብቃት ምዘና ለመስራት ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች አንዱ የፋይናንስ ሪፖርት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ቦርዱ የኩባንያዎችን ሙሉ ኦዲት ፋይናንስ ሪፖርት በማጣራት ጠንካራ የሂሳብ ሪፖርት እንዲያቀርቡ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም