አድዋ- የጥቁር ህዝቦች ታላቅ የድል ብስራት፤ የአንድነት ምልክትና የጀግንነት ልኬት ነው - ኢዜአ አማርኛ
አድዋ- የጥቁር ህዝቦች ታላቅ የድል ብስራት፤ የአንድነት ምልክትና የጀግንነት ልኬት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2016(ኢዜአ)፦ አድዋ- የጥቁር ህዝቦች ታላቅ የድል ብስራት፤ የአንድነት ምልክትና የጀግንነት ልኬት መሆኑን የካራማራ ጦርነት የሜዳሊያ ተሸላሚ መቶ አለቃ በቀለ በላይ ገለጹ።
በየካቲት ወር የተገኘው ትልቁ የአድዋ ድል የካቲትን የአፍሪካውያን ወር እንዲሰኝ አድርጎታል።
አፍሪካውያን በግፍ በሚረገጡበት፣ በባርነት በሚገዙበት፣ ቅኝ ገዥዎች ያሻቸውን ያለከልካይ በሚፈፅሙበት በዚያን ወቅት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች "እምቢኝ! ሀገሬን በቅኝ አላስገዛም" በማለት የቅኝ ገዢዎችን ህልም በአድዋ መና አስቀርተዋል።
ነጭ መሆን ሚዛን የሚደፋበት፤ ጥቁር ሆኖ መፈጠር አንገት የሚያስደፋበት ያ አስከፊ ጊዜ በአድዋ ድል ተሽሯል።
በመሆኑም አድዋ ለአንድ ዓላማ በጋራ በመሰለፍ ታላቅ የድል ብስራት የተገኘበት፤ የአንድነት ውጤትና የጀግንነት ምልክት ተደርጎ ዘለአለም የሚወሳ ነው።
የአድዋ ድልን በማስመልከት ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በካራማራ ጦርነት ባስመዘገቡት ጀብዱ የሜዳሊያ ተሸላሚው መቶ አለቃ በቀለ በላይ፤ የአድዋ ጀግኖች የድል ታሪክ ከአድዋ በኋላም በትውልድ ቅብብሎሽ የቀጠለ የኢትዮጵያ መገለጫ ስለመሆኑ ይናገራሉ።
አድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ድል ቢሆንም በተለይ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት የጋራ ማንነት በጎ መገለጫ ከማድረግ ይልቅ የድል ሽሚያ በሚመስል መልኩ አሳንሰነው ቆይተናል ብለዋል።
በአድዋ ተራሮች የውጭ ጠላትን መክተን ነጻነታችንን ማስከበራችንን ደጋግመን ስንናገር ብንደመጥም፣ ድሉን ለጋራ ከፍታችን ከመጠቀም ይልቅ የመለያየታችን ምንጭ እንዲሆን ሲሰራበት እንደነበርም አስታውሰዋል።
በዚህም ታላቁን ድል በሚመጥነው ልክ ለዓለም ተምሳሌት አድርጎ ማቅረብና ለሀገረ መንግስት ግንባታ ማዋል አለመቻሉን ገልጸዋል።
የአድዋ ጀግኖች ከሁሉም አቅጣጫ በመትመም በጋራ ያስመዘገቡትን ድል ለህብረ-ብሄራዊ አንድነትና የሀገር ገጽታ ግንባታ በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ አድዋን የመሰሉ ብዙ ታሪኮችን መስራት የሚገባት ምዕራፍ ላይ መሆኗን ጠቅሰው ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የገጠመችው ጦርነት ከድህነት ጋር በመሆኑ ሁሉም እንደ አድዋ ዘመቻ በአንድነት በመሰለፍ ድህነትን በመዋጋት ታሪክ መስራት አለበት ብለዋል።
በአዲስ አበባ የተገነባው የአድዋ ድል መታሰቢያም ከፍታችንን በሚገባ ማጉላት የሚያስችል ሀገር ከፍ ብላ የታየችበት ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም ከአድዋ ጀግኖች በመማር በወንድማማችነትና በእህትማማችነት ላይ የተገነባ ህብረተሰብአዊ መተሳሰር መፍጠር ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ገልጸዋል።
128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል የፊታችን ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት ይከበራል።