የዜጎችን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል በህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው - ዶክተር መቅደስ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል በህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው - ዶክተር መቅደስ ዳባ
አዲስ አበባ ፤ የካቲት 19/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዜጎቿን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል በህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኗን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
"የማህበራዊ እና ባህሪ ለውጥ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ 3ኛው ሀገር አቀፍ የማህበራዊ እና ባህሪ ለውጥ ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ቀናት በተለያዩ መርሃ-ግብሮች እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በጉባኤው ላይ ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ሀገራት የተውጣጡ ከ400 በላይ ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል ተብሏል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የተለያዩ የጥናትና ምርምር ተሞክሮዎች ለፖሊሲ ግብዓትነት ቀርበው የልምድ ልውውጥና የዕውቀት ሽግግር እንደሚደረግበት ተመላክቷል።
በዚሁ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ ኢትዮጵያ የዜጎቿን የጤና ሥርዓት ለማሻሻል በህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።
የዜጎችን ጤንነት በዘላቂነት ለመጠበቅ በቅደመ መከላከል፣ በግንዛቤ ፈጠራ እና በመሰረተ ልማት ግንባታ ዙሪያ ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር እሸቱ ግርማ በበኩላቸው የዜጎችን የበሽታ መከላከል ንቃተ ህሊና ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም የጤና ባለሙያዎችን ዕውቀት ማጎልበት የሚያስችሉ ስልጠናዎችን ጨምሮ ለፖሊሲ ግብዓትነት የሚያገለግሉ ጥናቶች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ከመድረኩ ጎን ለጎን በጤናው ዘርፍ ጥናትና ምርምር ላደረጉ ምሁራን፣ የግንዛቤ ፈጠራ ለሰሩ የጤና ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል።