ቀጥታ፡

ለዘንድሮው የሐጂ ጉዞ እስካሁን 5 ሺህ 628 ሁጃጆች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 19/2016 (ኢዜአ)፦ ለ1 ሺህ 445ኛው የሐጂ ጉዞ እስካሁን 5 ሺህ 628 ሁጃጆች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የጠቅላይ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንትና የሐጅ እና ኡምራ ዘርፍ ኃላፊ ሸኽ አብዱላዚዝ ሸኽ አብዱል ወሊ፣ ሌሎች የስራ ኃላፊችና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የስራ ሃላፊዎች የሐጅና ኡምራ ጉዞ የምዝገባ ሒደትን ጎብኝተዋል፡፡


 

ከጉብኝቱ በኋላ ገለፃ ያደረጉት ሸህ አብዱላዚዝ ሸኽ አብዱል ወሊ፤ በዘንድሮው የሐጅ ስነ ስርአት 13 ሺህ ሁጃጆች የመጓዝ እድል ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሐጅና ኡምራ ምዝገባ መጀመሩን ጠቅሰው እስካሁን 5 ሺህ 628 ሁጃጆች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ማዕከል ብቻ ይካሄድ የነበረው ምዝገባ ቀርቶ ዘንድሮ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች 27 ተጨማሪ የምዝገባ ጣቢያ ተከፍተው ቀልጣፋና የዘመነ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ምዝገባው ሊጠናቀቅ ስምንት ቀናት ብቻ ቀርተዋል ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ፓስፖርት ወይም የቀበሌ መታወቂያና ፎቶግራፍ በመያዝ በአቅራቢያቸው እንዲመዘገቡ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሪያድ ጀማል፤የሐጅና ኡምራ ምዝገባ ስርዓቱን ከማዘመን አንጻር ሰፊ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን ገልጸዋል።


 

በእለቱ ሲመዘገቡ ያገኘናቸው ሁጃጆችም አገልግሎቱ ፈጣንና ቀልጣፋ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም