ቀጥታ፡

በድሬዳዋና አካባቢዋ ማህበራዊ አገልግሎትና ኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የድርሻችንን እናበረክታለን - ትውልደ ኢትዮጵያዊያን

ድሬዳዋ፤  የካቲት 19/2016 (ኢዜአ) ፡- በድሬዳዋና አካባቢዋ ማህበራዊ አገልግሎትና ኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የድርሻቸውን ለማበርከት እንደሚሰሩ በተለያዩ የውጭ አገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ።

ከ30 አገራት የተውጣጡ ትውልደ ኢትዮጵያንና የውጭ አገራት ዜጎች "ዲያሎግ ሂዩማኒቲ" በሚል መሪ ሃሳብ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ከድሬዳዋ የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር መክረዋል።

ከትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ መካከል ለ40 ዓመታት በፈረንሳይ አገር የኖሩትና የኢትዮጵያ - ፈረንሣይ ወዳጅነት ማህበር ፕሬዚዳንት አህመድ አሊ ሰኢድ አንዱ ናቸው።

አህመድ አሊ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የተካሄደው ውይይት ህዝብን በማስተሳሰርና በማቀራረብ በማህበራዊ ልማቶች ላይ ዜጎች በያሉበት ቦታ ኃላፊነታቸው እንዲወጡ የሚያነሳሳ ነው።

ማህበራቸው በመላው ዓለም የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር በጤና፣ በትምህርት፣ በህፃናትና ሴቶች ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ  ለድሬዳዋ ተቋማት ድጋፎች ማበርከቱን አስታውሰዋል።

በተለይም የህክምናና ሌሎች መገልገያ ቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ ለወደፊቱም ባላቸው ዕውቀት፣ ሀብትና ገንዘብ በኢንቨስትመንት ስራ ውስጥ እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ- ፈረንሳይ ወዳጅነት ማህበር አመራር አባል ወይዘሮ ገነት ኃይለሥላሴ በበኩላቸው፤ ማህበራዊ ችግሮችን ከመፍታት በዘለለ ግዙፍ የውጭ ኢንቨስተሮች በድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ የሚሳተፉበት መንገድ የማመቻቸት ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በፈረንሳዊው ባለቤታቸው በኩል ከግዙፍ ኩባንያዎች ጋር ትስስር በመፍጠር ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ለማድረግ ከማህበረሰቡ ጋር የተካሄደው ውይይት እንዳነሳሳቸው ተናግረዋል።

ከአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት የመጡት ወይዘሮ አዜብ ዩሱፍ በበኩላቸው፤ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን ከሂዩሰተን ዩኒቨርስቲ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲፈጥሩ ለማድረግ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና በጤና ተቋማት ጉብኝታቸው ወቅት ያስተዋሏቸው ክፍተቶች እንዲፈቱ በዕውቀት፣ በገንዘብና ሰውን በማስተባበር የበጎ ፍቃደኝነት አምባሳደር ሆነው እንደሚሰሩ ነው ያወሱት።

በዴንማርክ የምትኖረው ኢትዮጵያዊቷ ሞዴል ፈቲሃ መሐመድ በበኩሏ የተካሄደው የማህበረሰብ ውይይት "ለጠንካራ ትስስር ወሳኝ ሚና ይጫወታል" ብላለች።

በድሬዳዋ የተደረገላቸው አቀባበልና መስተንግዶ አስደሳች መሆኑን ጠቅሳ፤ ስለኢትዮጵያ መልካም ነገሮች በሚጓዙበት ሁሉ ለመመስከር መዘጋጀቷን ገልጻለች።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች በአገርና በድሬዳዋ ማህበራዊ ልማቶች እያበረከቱ የሚገኙት አስተዋጽኦ የሚያበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።


 

በየዓመቱ ወደ ድሬዳዋ በመምጣት ያሉትን ችግሮች በመለየትና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር እያደረጉት ለሚገኙት ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

በቀጣይም በአገርና በድሬዳዋ ልማቶችና በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የጀመሯቸውን ተግባራት በማጠናከር አገራዊ የለውጥ ጉዞው እንዲሳካ መትጋት እንዳለባቸው ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው መጥተው አገራቸውን የጀመረቻቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን እንዲመለከቱና በዚያውም የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም