ኢትዮጵያ የተቃርኖ እሳቤዎችን ወደ ውይይትና ምክክር በማምጣት የጋራ መፍትሄ ማበጀት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የተቃርኖ እሳቤዎችን ወደ ውይይትና ምክክር በማምጣት የጋራ መፍትሄ ማበጀት ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የተቃርኖ እሳቤዎችን ወደ ውይይትና ምክክር በማምጣት የጋራ መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባ ተገለጸ።
በዚህ ረገድ ላለፉት ዓመታት ሲካሄዱ የነበሩ የአዲስ ወግ የውይይት መድረኮች በኢትዮጵያ መሰረታዊ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት መሰረት እንደሆኑ የተለያዩ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የተቃርኖ እሳቤዎችን በውይይትና ምክክር ለማቀራረብ የሚንቀሳቀሰው የዴስቲኒ ኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ ንጉሱ አክሊሉ፤ በኢትዮጵያ የውይይት፣ የምክክርና መግባባት ባህል መዳበር እንዳለበት ይገራሉ።
የተለያዩ ሃሳቦችን ወደ መድረክ በማምጣት መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት በመንግስት ተነሳሽነት ሲካሄድ የቆየው አዲስ ወግ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአዲስ ወግ መድረኮች በተሳታፊዎች ስብጥር፣ በርዕሰ ጉዳዮች መረጣ እንዲሁም በፖሊሲ ተጽዕኗቸው ሲመዘኑ ትልቅ ዋጋ የሚሰጣችው ነበሩም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሀገሪቷ ሁለንተናዊ ችግሮች መፍትሔ እንደሚሆን የተናገሩት አቶ ንጉሱ፤ ዴስቲኒ ኢትዮጵያ ለምክክሩ ስኬት የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
በአዲስ ወግ መድረኮች ላይ ሲሳተፉ የነበሩት የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ሠብለ ኅይሉ፤ አዲስ ወግ በአካታችነት ለሀገር የሚጠቅሙ መልከ ብዙ ዕይታዎች የተንጸባረቁበት መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ የሚካሄዱ የውይይትና የምክክር መድረኮችም የአዲስ ወግን መልካም ተሞክሮዎች ሊሰንቁ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ የተቃርኖ እሳቤዎችን ወደ ውይይትና ምክክር በማምጣት የጋራ መፍትሄ ማበጀት ይገባል ሲሉም አስተያየት ሰጭዎቹ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረሥላሴ፤ እንደ አዲስ ወግ አይነት መድረኮች ፖለቲካዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መሰረት መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከስሜታዊነትና ጥላቻ ይልቅ በመረጃና ዕውቀት ላይ የተመሰረቱ ውይይቶችን በማዳበር የጋራ መፍትሔዎችን ማምጣት ይገባል ብለዋል።
አዲስ ወግ እና መሰል የውይይት መድረኮችም ለሀገራዊ ምክክር ሂደት አጋዥ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።