የአዲስ ወግና መሰል የውይይት መድረኮች የኢትዮጵያን ስብራቶች ለመጠገን የሚበጁ ናቸው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ ወግና መሰል የውይይት መድረኮች የኢትዮጵያን ስብራቶች ለመጠገን የሚበጁ ናቸው- ዶክተር ለገሰ ቱሉ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2016(ኢዜአ)፦የአዲስ ወግና መሰል የውይይት መድረኮች የኢትዮጵያን ስብራቶች ለመጠገን የሚበጁ በመሆናቸው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ ገለጹ።
ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ሲካሄዱ የነበሩ የአዲስ ወግ መድረኮችን የሰነደ መፅሐፍ በትናንትናው እለት ተመርቆ ለንባብ መብቃቱ ይታወቃል።
የአዲስ ወግ መድረክ መጠናቀቁን ተከትሎም ቅኝት የተሰኘ ሌላ ሀገራዊ መድረክ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሚቀጥል መሆኑ ተገልጿል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሠ ቱሉ፤ ለአምስት ዓመታት በተካሄደው የአዲስ ወግ የውይይት መድረኮች የተንሸራሸሩ ሃሳቦች ምክንያታዊ ማህበረሰብ ለመገንባት የላቀ ሚና ነበራቸው ብለዋል።
በመድረኮቹ በማያግባቡ ጉዳዮች መግባባት ላይ ለመድረስ የተሞከረበት እንደነበር አስታውሰው የመንግስትን ትኩረት የሳቡ በርካታ ጠቃሚ ሃሳቦች የቀረቡበት እንደነበርም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ስብራቶች በመኖራቸው መንግስት ስብራቶችን ለመጠገን ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የአዲስ ወግና መሰል የውይይት መድረኮች የኢትዮጵያን ስብራቶች ለመጠገን የሚደረገውን ጥረት የሚያግዙ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ነው ያሉት።
አዲስ ወግ ቁልፍ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትና የጋራ ዕይታ ለመፍጠር የታለመላችው መድረኮች እንዲፈጠሩ ማስቻሉንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬተር መሀመድ እድሪስ፤ አዲስ ወግ የሃሳብ ብዝሃነትና የሀገር ምስል ያሳየ፣ ጥያቄዎች የሚቀርቡበትና ሙያዊነትን ጠብቆ ሲካሄድ እንደነበር ገልጸዋል።
የአዲስ ወግ የውይይት ጭብጦች በመገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ በስፋት ተደራሽ በመደረጋቸው ለሀገር ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል።
ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የዘለቀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ ከፖሊሲ ግብዓትነት ባለፈ የውይይት ባሕል እንዲዳብር አስተዋጽኦ ማበርከቱ ይታወቃል።