በጎንደር ከተማ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻያ ግንባታ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻያ ግንባታ እየተካሄደ ነው
ጎንደር ፤ የካቲት 19 / 2016 (ኢዜአ)፡- በጎንደር ከተማ ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማሻሻያ ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሸ ደሴ በከተማው እየተገነቡ የሚገኙ የትምህርት ተቋማትን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በወቅቱ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ነጻነት መንግስቴ እንደተናገሩት፤ በከተማው ከሚገኙ 57 የመንግስት ትምህርት ቤቶች መካከል 87 በመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው፡፡
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል በተጀመረው ንቅናቄም በ12 ነባር ትምህርት ቤቶች ለማማር ማስተማር ስራው ምቹ ለማድረግ ከ60 በላይ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም ቀደም ሲል በጭቃና እንጨት የተሰሩ ሦስት ትምህርት ቤቶችን ገፅታ ለመቀየር የማስፋፊያ ግንባታ መጀመሩንም ጠቅሰዋል፡፡
የትምህርት ቤቶቹ የግንባታ ስራ እየተካሄደ የሚገኘው በከተማ አስተዳደሩ፣ በአማራ ልማት ማህበር፣ በዳሽን ቢራ አክሲዮን ማህበር፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲና በወጭ በሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች የገንዘብ ድጋፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአዘዞ ክፍለ ከተማ በ65 ሚሊዮን ብር ወጪ 12 የመማሪያ ክፍሎች ያሉት ሁለት የመማሪያ ህንጻዎች አስገንብቶ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የገለጹት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ልጃለም ጋሻው ናቸው፡፡
የህንጻዎቹ ግንባታ ከመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ አንድ ቤተ መጻህፍት፣ ሁለት ቤተ ሙከራና አንድ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል በውስጡ ማካተቱንም ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የከተማው ትምህርት ቤቶች የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታና የትምህርት ጥራት ጉድለቶችን በመረጃ የተደገፈ ጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን ምክረ ሃሳቦችን ለከተማ አስተዳደሩ በማቅረብ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሸ ደሴ በበኩላቸው፤በትምህርት ጥራት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመሻገር የአጋር አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በከተማ አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ የትምህርት ዘርፍ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ክልሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ ቃል ገብተዋል፡፡
በጎንደር ከተማ በትምህርት ዘመኑ በከተማው በሚገኙ 57 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ከከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡