ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ አገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያፋጠነ  ነው-ዶክተር ዮናስ አዳዬ

ሶዶ እና ዲላ የካቲት 19/2016  (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እያፋጠነ መሆኑን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በወላይታ እና በጌዴኦ ዞኖች በሀገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የማህበረሰብ ተወካዮችን ለመለየት ያዘጋጀው መድረክ በወላይታ ሶዶ እና በዲላ ከተሞች እየተካሄደ ነው። 

በወላይታ ሶዶ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ የተገኙት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ እንዳሉት፣ ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክሩን ለማካሄድ እያከናወናቸው ያለው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በማፋጠን ላይ ነው።

ኮሚሽኑ እስካሁን ባደረገው እንቅስቃሴም በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተሳካ የማህበረሰብ ተወካዮች መረጣ ማከናወኑን በማሳያነት ገልጸዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ወላይታን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ዞኖች የማህበረሰብ ተወካዮች ልየታ እንደሚካሄድ አመልክተዋል። 

አገራዊ ምክክሩ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ዴሞክራሲያዊ ስርዓተ ግንባታ እንዲጎለብት ከማስቻል ባለፈ በአገሪቱ የውይይት ባህልን ለማዳበር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለዚህም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ተሳታፊዎች ለመምረጥ የሚያስችል ግልጽና ገለልተኛ አሰራር በመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በተወካዮቻቸው በኩል በአገራዊ ምክክሩ እንዲሳተፉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎች ይወክሉናል ላሏቸው አካላት የተለያዩ አገራዊ አጀንዳዎችን በመስጠት ሀሳብና ጥያቄያቸው እንዲደመጥ የሚደረግበት ሂደት መሆኑንም አስረድተዋል። 

ለምክክሩ ውጤታማነት በፌዴራል፣ በክልሎች እንዲሁም በከተማ መስተዳደሮች በሚደረጉ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራዎች ላይ ጉልህ ድርሻ የሚኖራቸው አካላት መካተታቸውንና ተገቢውን ተሳትፎ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ ኮሚሽኑ በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል። 

በተመሳሳይ ዜና ኮሚሽኑ በጌዴኦ ዞን የማህበረሰብ ተወካዮችን ለመምራጥ ያዘጋጀው መድረክ በዲላ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቁ ጌጡ በወቅቱ እንዳሉት መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልዩነት እና አለመግባባቶች ይስተዋላሉ።


 

ኮሚሽኑ በቀጣይ ህዝባዊ ውይይቶችን በማዘጋጀት የሀሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶች ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራትን እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

የውይይት መድረኮቹ በውክልና እንደሚካሄዱ የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በአሁኑ ወቅትም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰብ ተወካዮችን የመምረጥ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም በውይይቱ ተሳታፊ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳዎቻቸውን የሚያቀርቡላቸው ተወካዮችን በአግባቡ መምረጥ እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።

በጌዴኦ እና በወላይታ ዞን የሚካሄደው የማህበረሰብ ተወካዮች መረጣ ለቀጣዮቹ አራት ቀናት እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።

የተወካዮች መረጣ አካታችነት፣ ግልፀኝነት፣ አሳታፊነትና ተአማኒነትን ባገናዘበ መልኩ እንደሚካሄድ ታውቋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም